አምዶች
የቅርብ ዜና
አብን የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን አዎንታዊ ጎኖች ማደነቁንና የታዩ ጥሰቶችን መቃወሙን ገለጸ በግብፅ የመጀመሪያው የኒውክሌር ጣቢያ ግንባታ ላይ ጉድለት መገኘቱ ውዝግብ አስነሳ ኢራን በሆርሙዝ የባህር ወሰን ላይ ያላትን ይዞታ እያጣች መሆኑ ተገለጸ ደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ልምምዱ «እንደታቀደው ይቀጥላል» ስትል የትራምፕን ሃሳብ ውድቅ አደረገች የአዲስ አበባ ባለቤትነት ውዝግብ፡ በሀገራዊ ምክክሩና በፖለቲካው መድረክ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል የጋራ ማረጋገጫ ቡድን አባላት ምርጫና የአሰራር ደንቦች አዲስ ውዝግብ ማስነሳታቸው ተገለፀ በሃይማኖት ጉዳዮች እና ሰላም ግንባታ አጀንዳዎች ላይ ሙሉ መግባባት ተደረሰ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውሳኔን ተከትሎ የአንበሳ ባንክ ሙሉ በሙሉ አዲስ የዳይሬክተሮች ቦርድ መረጠ የመንግሥት “ዜሮ ተፈናቃይ” መርሐግብር እና የተሸፈኑ እውነታዎች የአሜሪካ በግብፅ ላይ ያተኮረ አካሄድ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ስትራቴጂ እያበላሸው ነው — ብሌን ማሞ ዲሪባ አብን የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን አዎንታዊ ጎኖች ማደነቁንና የታዩ ጥሰቶችን መቃወሙን ገለጸ በግብፅ የመጀመሪያው የኒውክሌር ጣቢያ ግንባታ ላይ ጉድለት መገኘቱ ውዝግብ አስነሳ ኢራን በሆርሙዝ የባህር ወሰን ላይ ያላትን ይዞታ እያጣች መሆኑ ተገለጸ ደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ልምምዱ «እንደታቀደው ይቀጥላል» ስትል የትራምፕን ሃሳብ ውድቅ አደረገች የአዲስ አበባ ባለቤትነት ውዝግብ፡ በሀገራዊ ምክክሩና በፖለቲካው መድረክ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል የጋራ ማረጋገጫ ቡድን አባላት ምርጫና የአሰራር ደንቦች አዲስ ውዝግብ ማስነሳታቸው ተገለፀ በሃይማኖት ጉዳዮች እና ሰላም ግንባታ አጀንዳዎች ላይ ሙሉ መግባባት ተደረሰ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውሳኔን ተከትሎ የአንበሳ ባንክ ሙሉ በሙሉ አዲስ የዳይሬክተሮች ቦርድ መረጠ የመንግሥት “ዜሮ ተፈናቃይ” መርሐግብር እና የተሸፈኑ እውነታዎች የአሜሪካ በግብፅ ላይ ያተኮረ አካሄድ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ስትራቴጂ እያበላሸው ነው — ብሌን ማሞ ዲሪባ
ነፃ ሃሳብ / ይፋዊ ንግግሮች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ

በያፌት ግርማ | July 7, 2026
🔒 Log in or create an account to earn rewards for reading this article!

የተከበራችሁ የምክር ቤት አባላትና የሀገራችን ህዝቦች፤

 

ከሁሉ አስቀድሜ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት ድርጅት፣ ህዝብ እና መንግስት የሰጣችሁን አደራ በታላቅ የሃላፊነት ስሜት ስታገለግሉ ለቆያችሁ እና በሚቀጥለው የምክር ቤት ዘመንም በተለያየ ደረጃ የመንግስት አካል ሆናችሁ ለምታገለግሉ የብልጽግና ፓርቲ አባላት ላበረከታችሁት አገልግሎት ድርጅታችንና መንግስት ከፍተኛ ክብርና ምስጋና አለው።

 

በተጨማሪም በተፎካካሪ ፓርቲዎች ተወክላችሁ ላለፉት አምስት ዓመታት በእውቀታችሁ፣ በአቅማችሁና በመሻታችሁ ልክ ሀገራችሁን ያገለገላችሁ፣ በዚህ ምክር ቤት ውስጥ ድምጻችሁን ያሰማችሁ—ለምሳሌ ክቡር አቶ ባርጤማ ፈቃዱ እና የኢዜማ ፓርቲ አባላት በሙሉ፣ ክቡር አቶ ደሳለኝ ጫኔ እና የአብን ፓርቲ አባላት በሙሉ፣ ዶክተር መብራቱ አለሙ እና ሌሎችም ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የግል ተወዳዳሪዎች—የህዝብ፣ የፓርቲያችንና የኛ አመለካከት ብላችሁ ላራመዳችሁት ሃሳብ፣ ጥያቄና አስተያየት በሙሉ ከፍ ያለ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ። 

 

አንዳንዶቻችሁ በሚቀጥለው ምክር ቤት ከኛ ጋር የማትቀጥሉ መሆኑን የዘንድሮው ምርጫ ያሳየ ቢሆንም፣ ክቡር አቶ ደሳለኝ ጫኔ ያደረጉት ንግግር የመጨረሻ እንዳይሆን የመንግስት ምኞት ነው። ከምክር ቤት ውጪም ቢሆን እናንተን አካቶ፣ ሁላችንም የዚች ሀገር ልጆች በመሆናችን ኢትዮጵያን በጋራ እንድናለማና እንድናገለግል በተከበረው ምክር ቤት ፊት ጥሪ ማቅረብ እፈልጋለሁ። ይህንን ካልኩ በኋላ፣ ምርጫንና ሰላምን በተመለከተ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እወዳለሁ። 

 

የዘንድሮው ምርጫ ህግና ፈቃድ ላለው ለማንኛውም የፖለቲካ አካል ትልቅ ትምህርት የሰጠ፣ ዘርፈ-ብዙ መልዕክቶችን በውስጡ የያዘና የኢትዮጵያን ህዝብ ውስብስብና የረጅም ዘመናት ድልብ የማህበራዊ ካፒታል (Social Capital) ባለቤት መሆኑን ያረጋገጠ ነው። ላይ ላዩን የምንናገረውና በውስጥ ያለው የህዝቡ እምነት ምን ያህል የተለያየ መሆኑን ያየንበት ሂደት ነበር። 

 

ይህ ምርጫ ከእስካሁኖቹ የሚለይበት አንድ ሁነኛ ባህሪ አለው። «አትመዝገቡ» ተብለው «የለም እንመዘገባለን» ብለዋል። «አትደግፉ፣ አትምረጡ» ተብለዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን እነዚህን ሁሉ እገዳዎችና ማስፈራሪያዎች ሳይቀበል፣ ከንጋት እስከ ሌሊት በነቂስ ወጥቶ፣ ከ50 ሺህ በላይ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ታይቶ በማይታወቅ ቁጥር ተሰልፎ ያሳየው ተጋድሎ ትልቅ ትምህርት የወሰድንበት ነበር።

 

ከዚህ ቀደም የሚፎካከሩ ኃይሎች በሃሳብ፣ አልፎ አልፎም በጉልበት ይጠቃቁ ነበር፤ ዘንድሮ ግን የሚፎካከሩ ኃይሎች ሳይሆኑ እራሱ ምርጫው የጥቃት ኢላማ ነበር። ምርጫው እንዳይከወን እንደ አንድ ታርጌት ተወስዶ ተሰርቶበታል። ምክንያቱም የእኛን ባንዳዎች የሚያሰማሩና የሚልኩ ኃይሎች በሙሉ ምርጫ አይወዱም። ማሸነፍ፣ ከፈተና መሻገርና ሀገር የማጽናት ልምድ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን እነዚያን ፍላጎቶች ሳይቀበል በተባበረ ክንድ ላደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ክብር ይገባዋል።

 

ጀርመኖች «ሃሳብ ሲሞት፣ ንግግርና ውይይት ሲሞት ጉልበት አለሁ ይላል» ይላሉ። በሀገራችንም «ውሃ ዝቅ ሲል ይሸታል፤ ሰው ሲደክም ደግሞ ኩራትና ፉከራ ያበዛል» የሚል አባባል አለ።

 

«ማድረግ አትችሉም፣ አይሳካም» የሚለው የብዙ ኃይሎች ፍላጎት ቢሆንም፣ ኢትዮጵያውያን ግን በሰሜንም፣ በደቡብም፣ በምስራቅም፣ በምዕራብም በአንድ ድምፅ «ጽንፈኝነት፣ ባንዳነትና ዘረኝነት አንፈልግም፤ ምኞታችን ተባብረን የጋራ ሀገራችንን ማጽናትና ማበልጸግ ነው» የሚለውን ታላቅ ድምፅ አስተጋብተዋል።

 

አዛውንቶችና በሽተኞች በድጋፍ ወጥተው መርጠዋል። እነሱ የመረጡት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ስለመኖራቸው እርግጠኛ ሆነው ሳይሆን፣ በነሱ ድምፅ ሀገር መጽናትና የልጆቻቸው ቀጣይነት መረጋገጥ ስላለበት ነው። እናቶች ልጆቻቸውን አዝለው፣ ዜጎች የጥይት ድምፅ እየሰሙ ሸብረክ ሳይሉ ነው የመረጡት። ይህንን እንደ ትልቅ አደራና ታላቅ ኃላፊነት ነው የምንወስደው።

 

ህዝቡ ለእኛ የሰጠን መልዕክት ግልፅ ነው፦ «ጅምራችሁ መልካም ነው፣ ስርአታዊ ሌብነት መጥፋቱን እንደግፋለን፤ አሁንም ግን በውስጣችሁ ሌቦች ስላሉ ሌብነትን አጥርታችሁ፣ አገልግሎትን አሻሽላችሁ የጸናች ሀገር አስረክቡን» የሚል ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የሰጠን ባዶ ቼክ (Blank Check) ነው። በዚህ ቼክ ላይ መልካም ስም፣ መልካም ስራና መልካም ውጤት መዝራት የእኛ ኃላፊነት ነው። ይህንን ቼክ በአግባቡ ካልተጠቀምንበት፣ ህዝቡ ጥይት ሳይፈራ እንደመረጠን ሁሉ ጥይት ሳይፈራ የተቃርኖ እርምጃ መውሰድ እንደሚችልም ጭምር አይተናል።

 

ዲሞክራሲ ከኛ ወዲያ ለሚሉ ሀገራት ጭምር አርአያ በሆነ መልኩ፣ የብልጽግና ፓርቲ ገና ከስድስት ወራት በፊት በነበረው ውይይት «ብልጽግና ከ85 ፐርሰንት በላይ ወንበር አይወዳደርም፤ 15 ፐርሰንቱ ሙሉ በሙሉ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት ይተው» ብሎ ወስኖ ነበር። በድፍን አፍሪካ 15 ፐርሰንት አልወዳደርም የሚል ገዢ ፓርቲ መኖሩን እጠራጠራለሁ። ይህንንም ያደረግነው ብዙ ድምጾች እንዲሰሙና እንዲሳተፉ ፍላጎት ስላለን ነው። በሚቀጥለው አካታች ብሔራዊ ምክክር (Inclusive National Dialogue) ላይም በስልጣን ላይ ያለ መንግስት ማክሲመም ሁለት ተርም (ከሁለት የሥራ ዘመን በላይ) መቆየት የለበትም የሚል አጀንዳ ይዘን ቀርበናል።

 

ሰላምን በተመለከተ የተነሱት ሃሳቦች በሙሉ ገንቢ ናቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ታፍነው የኖሩ ችግሮችና ሃሳቦች፣ አሁን የተሻለ ስፔስና የሶሻል ሚዲያ ቴክኖሎጂ ሲመጣ መውጣታቸው የሚጠበቅ ነው። እነዚህን በትዕግስት ማስተናገድ ዘላቂ የፖለቲካ አውድ ለመፍጠር ያግዛል።

 

ባለፉት ዓመታት እኔ ራሴ ከህዝብ፣ ከአባቶች፣ ከመንግስት ሰራተኞች፣ ከሃኪሞች፣ ከመምህራንና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር 25 መድረኮችን፣ ፓርቲያችን ደግሞ በየደረጃው ከ4,000 በላይ መድረኮችን ፈጥሯል። ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽንም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ያሳተፈ የሣር ሥር (Grassroots) ውይይት አድርጓል።

 

ነዚህ ውይይቶች ምን አገኘን ካላችሁ፦ የማህበረሰብ ግጭቶች በእጅጉ ቀንሰዋል። በአማራና ኦሮሞ፣ በሱማሌና ኦሮሞ፣ በጌዲዮና ሲዳማ፣ በሃይማኖቶች መካከል የነበሩ ግጭቶች ቀንሰዋል። አሁን ያለው ችግር ብሔርና ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው ሀገር እንዳትረጋጋ የሚሹ፣ ገንዘብና ጊዜያቸውን አጥፍተው ባንዳ የሚያሳድዱ የውጭ ኃይሎችና የውስጥ ተላላኪዎቻቸው የሚፈጥሩት ግጭት ነው።

 

የጸጥታና የህግ አስከባሪ ተቋሞቻችን (Law Enforcement Agencies) በቁጥር፣ በብቃትና በቴክኖሎጂ መገመት ከሚቻል በላይ እያደጉ መጥተዋል። ነገር ግን የሽፍቶች ባህሪ የኮንቬንሺናል (መደበኛ) ጦርነት ባህሪ ስላልሆነ፣ ህዝባችን ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በትብብር መስራት ይጠበቅበታል። እንደ ቦኮ ሃራም ያሉ ቡድኖች በናይጄሪያ ለዓመታት እንደሚቆዩት ሁሉ፣ የሽፍታ ባህሪው መደበቂያ መፈለግ ቢሆንም፣ የህዝብና የመንግስት ትስስር ሲጠነክር እየጠፉ መሄዳቸው ግን ጥርጥር የለውም።

 

የኦሮሚያም ሆነ የአማራ ክልል የታጠቁ ኃይሎች ተነጋግረውና ተደራድረው በሰላም እንዲመለሱ ጥሪያችንን እናጠናክራለን፤ ምክንያቱም ግጭት ወደ ድል አይወስድም።

 

የፕሪቶሪያው ስምምነት ብዙ ውጤት ያስገኘ የሰላም ስምምነት ነው። መንግስት ካሸነፈ በኋላ እንኳ ተሸናፊውን አካል እኩል አስቀምጦ ያወያየበት፣ የታጠቁ ኃይሎችን መልሶ ለማቋቋም ድጋፍ የሰጠበት ሂደት ነው። በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሟል፣ ከ6 ሺህ በላይ የታጠቁ ኃይሎች ተቀንሰዋል፣ ምርኮኞች ተፈትተዋል፣ የበረራና የቴሌኮም አገልግሎቶች ተለቀዋል። ለሰላም ሲባል ንብረቶቻቸውን ጠብቀን አስረክበናል።

 

ነገር ግን በትግራይ ካሉ አንዳንድ ኃይሎች በየቀኑ ትንኮሳዎች ይፈጸማሉ። እንዲያውም የትግራይ ወጣቶች በጉልበት ታፍሰው ሱዳን ላለው ጦርነት ተሽጠው በማያውቁት ጉዳይ ህይወታቸውን እያጡ ይገኛሉ። የትግራይ ህዝብ የችግሩ ባለቤት ሳይሆን የችግሩ ገፈት ቀማሽ ነው። ዛሬ በትግራይ ውስጥ ከሚኖር ትግራዋይ ይልቅ በደሴ፣ በጎንደር፣ በባህርዳር፣ በአዲስ አበባ፣ በቢሾፍቱና በሀዋሳ ያለው ትግራዋይ የተሻለ ሰላም አለው።

 

ልክ እንደዚሁ፣ «ለአማራ ህዝብ እንታገላለን» በሚሉ ኃይሎች አካባቢ ካለው አማራ ይልቅ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በሱማሌ ያለው አማራ የተሻለ ሰላም አለው። «ለኦሮሞ እንታገላለን» በሚሉ አካባቢዎች ካለው ኦሮሞ ይልቅ በአማራና በአፋር ያለው ኦሮሞ የተሻለ ሰላም አለው። ዜጎች በገዛ ልጆቻቸው እየታመሱ ይገኛሉ። ህዝብ አስለቅሶ የሚደረግ ትግል የትም እንደማያደርስ ከታሪክ መማር ያስፈልጋል።

 

በትግራይና በሀገራችን ያለው የፖለቲካ አውድ «የመጥረቢያ ፖለቲካ» ሰለባ ሆኗል። መጥረቢያ ሶስት አክተሮች አሉት፦

1. ከብረት የሚሰራው የተሳለው ስለት (መቁረጫው)

2. እዛ ውስጥ የሚገባው ተጣሞ የተሰራው እንጨት (እጀታው)

3. እንጨቱን ይዞ የሚቆርጠው ዋናው አካል (ባለቤቱ)

ብረቱ (ስለቱ) የራሱ አላማ የለውም፣ የእንጨቱን አላማ ይፈጽማል፤ እንጨቱም ቢሆን የያዘውን እጅ ፍላጎት ነው የሚመልሰው። ህወሃት እንደ መጥረቢያው ብረት ነው፤ መያዣው እንጨት ደግሞ እንደ ሻቢያ ነው፤ ዋናው አዛዦችና ባለጉዳዮች ግን ሌሎች የውጭ ኃይሎች ናቸው። ከመጥረቢያውና ከእንጨቱ ጋር ብቻ ብንጋጭ፣ ከጀርባው ያለው አዛዥ እስካለ ድረስ ዘላቂ ሰላም አይመጣም። ምክሬ፣ የኢትዮጵያ ሰላም ለነሱም ጭምር የሚጠቅም መሆኑን ተገንዝበው እንዲመለሱ ነው። የሀገራችንን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ትንኮሳ ከመነሻው ለመከላከል የሚያስችል ሙሉ ቁመና እንዳለን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።

 

ባለፉት ዓመታት «ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው፣ አለቀላት» ይባል ነበር። እኔ አሁንም የምላችሁ ኢትዮጵያ አትወድቅም፤ የወደቁትን ታነሳለች፣ የተኙትን ታነቃለች። ወደ ብልጽግና ጎዳና መጓዟንም ትቀጥላለች።

 

ብሔራዊ ምክክርን በተመለከተ፣ ኮሚሽኑ ሃሳቦችን አቀናብሮ ያቀርብልናል፤ እኛም ተወያይተን ጠቃሚውን እናጸድቃለን። ምንም የሚፈጠር የጸጥታ ስጋት የለም።

 

ባለፈው ምርጫ ካሸነፍን በኋላ የበዓለ-ሲመት ድግስ ደግሰን እንግዶችን ጋብዘን ነበር። በሚቀጥለው ጊዜ ግን ያንን አይነት ጊዜ ማባከን አያስፈልግም ብዬ አምናለሁ። ህዝቡ ስራ ስሩልን ብሎ መርጦናል፤ ፓርላማው ጠዋት ስራውን እንደጨረሰ ወዲያው ወደ ስራ መግባት ነው እንጂ እንግዳ በመቀበልና በመሸኘት ጊዜ ማጥፋት የለብንም። የሚጋበዝም፣ የሚደገስም የለም፤ ቡናችንን አፍልተን ፈንድሻችንን ቆልተን ስራችንን እንቀጥላለን።

 

ኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ሀገር ናት። ሀገር በኢንፍራስትራክቸር ብቻ አትገነባም፤ ማህበራዊ እሴቶችና ተቋማት (Supra-structure) ያስፈልጉናል። በሀገራችን 90% የሚሆነው ህዝብ የሚከተላቸው ሃይማኖቶች የተቀራረቡ ናቸው፤ ለሁሉም አዳምና ሔዋን እናትና አባት ናቸው፣ አብርሃም አባት ነው።

 

በአለም ላይ ያሉ ግጭቶች አራት መንስኤዎች አሏቸው፦

1. ብሔር፣ ሃይማኖትና ርዕዮተ-ዓለም

2. የኢኮኖሚ የበላይነት ፍላጎት

3. የበላይ (Superior) የመሆን ስነ-ልቦና

4. ግዛት ማስፋፋት

 

አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ፍላጎቶች ተደብቀው የሚወጡት በሃይማኖትና በብሔር ጥላ ስር ነው። ነገር ግን እስልምናም ሆነ ክርስትና የሰላም እምነቶች እንጂ የግጭት አይደሉም። ለዚህ ማረጋገጫዋ ኢትዮጵያ ናት። ሙስሊሞች በብዛት ባሉበት ክርስቲያኖች አዋጥተው ቤተክርስቲያን ይሰራሉ፤ ክርስቲያኖች በብዛት ባሉበትም ሙስሊሞች ተደግፈው መስጂድ ይሰራሉ። በጥናታችን መሰረት፣ ከ50% በላይ የሙስሊም ቁጥር ባለባቸው വረዳዎች ውስጥ ከ10 ሺህ በላይ አብያተ ክርስቲያናት አሉ። ግጭት የሚሰማው በጥቂት ቦታዎች ላይ ብቻ ነው።

 

ነውጠኞች ክብሪትና ጭድ ይዘው ይለኩሳሉ፤ ጀሌዎቻቸው ደግሞ እዚህ አዲስ አበባ ተቀምጠው ቤንዚን እያረከፈከፉ እሳቱን ያራግባሉ። ለኳሽና አራጋቢ ማዶ ለማዶ ተቀምጠው ችግሩን የእምነት መልክ ለመስጠት ይሞክራሉ።

 

የሰሞኑን የአርሲ ግጭት ብንወስድ፣ የምርጫውን ሂደት ለማደናቀፍ የታቀደ የሽፍቶች ጥቃት ነበር። አዲስ አበባ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር ቦምብና ክላሽ ስንይዝ ነበር። ጎንደር ላይ ተማሪዎች ቴሌቪዥን እያዩ ቦምብ ተጥሎባቸዋል። በአርሲ በነበረው ግጭት ህይወታቸው ያለፈው 11 ሰዎች ናቸው፤ ከነዚህም ውስጥ ስምንቱ (8) ሚሊሻዎችና ፖሊሶች ህዝቡ እንዳይገደል ተፋልመው ህይወታቸውን የገበሩ ጀግኖች ናቸው። የነሱን መስዋዕትነት ማራከስ አሳፋሪ ነው። በዚያ ግጭት የሞቱት ንጹሃን ውስጥ ሙስሊሞችም አሉበት። ውጊያው የእምነት ሳይሆን የሽፍቶች ጥቃት ነው። በዚህ ጉዳይ የተሳተፉ 22 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለዋል፤ የተፈናቀሉትም 90% ተመልሰዋል።

 

እዚህ አዲስ አበባ ተቀምጣችሁ ጫት እየቃማችሁ በሶሻል ሚዲያ የምታራግቡ ሰዎች ጥንቃቄ አድርጉ! እዚህ ሆኖ ባላጣራው ጉዳይ «እስላም ነው፣ ክርስቲያን ነው፣ አማራ ነው፣ ኦሮሞ ነው» እያለ የግሩፕ ጨዋታ የሚጫወተውንና እዚያ የሚጋጨውን ሰው ለይተን እናውቃለን። ይህ ስለምንጎዳ ጥንቃቄ ቢደረግ መልካም ነው።

 

ለትምህርት ጥራት የሚነሱ ሃሳቦች በጣም ጠቃሚ ናቸው። ከመንግስታችን የስራ መስኮች እጅግ ስኬታማው የትምህርት ዘርፍ ነው። መላው ፖሊሲው የመንግስታችን ቢሆንም፣ ይህንን ፖሊሲ በተግባር እያስፈጸሙ ያሉት የኢዜማው አባል ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ናቸው። የመንግስትን ፖሊሲ በታማኝነት ለማስፈጸም ደፋ ቀና እያሉ በርካታ ውጤት እያመጡ በመሆኑ ምስጋና ይገባቸዋል።

 

ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ህዝብ እንዲያዋጣ ተደርጎ በሁሉም ክልሎች ሞዴል ቦርዲንግ ሃይስኩሎች እየተገነቡ ነው። በግጭት የወደሙ ትምህርት ቤቶች እየተጠገኑ፣ መጽሐፍት እየታተሙና በቴክኖሎጂ የታገዘ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ ነው።

 

ባለፉት ሰባት ዓመታት 35,000 መዋለ-ህጻናት (Kindergarten) የገነባ መንግስት ነን። ይህንን በየትኛውም ሀገር ታሪክ አታገኙትም። እነዚህ ህጻናት አሁን ምርጫ እንደማይመርጡን፣ ፌስቡክ ላይ ላይክ እንደማያደርጉና ዩቱብ ላይ እንደማይናገሩ እናውቃለን፤ ነገር ግን ከ20 ዓመት በኋላ የዚች ሀገር ህልውና እነሱ መሆናቸውን ስለምናውቅ፣ ኢንቨስትመንታችን ለአጭር ጊዜ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ አርቆ አሳቢነት የተደረገ ነው።

እርግጥ ነው፣ አንድን ልጅ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ አምስት ዓመት ሙሉ አስተምረን ውጤቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማወቅ ከባድ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ሂደቱ ተስፋ ሰጪ ነው።

ለምሳሌ ያህል፣ ከ"መደመር" መጽሐፍ ሽያጭና ከመሰል የገቢ ምንጮች ብቻ የተገኘውን ጥሬ ገንዘብ በመጠቀም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት (የኦፊስ ኃላፊዎች) በሁሉም ክልሎች 35 ሞዴል ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ገንብቷል። የኢትዮጵያ ዘመናዊ መንግሥት ከተመሰረተበት ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ፣ በአንድ የጽሕፈት ቤት አቅም ብቻ 30 እና 35 ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አያውቁም። ይህንን ትልቅ ውሳኔ እና ቁርጠኝነት ማራከስ አይቻልም። አሁን በየቦታው እየገነባናቸው ያሉትን እነዚህን ሞዴል ሃይስኩሎች፣ ወደፊት ማደሪያ (ዶርሚተሪ) ብንጨምርባቸው በቀላሉ ወደ ቦርዲንግ ትምህርት ቤት ማደግ የሚችሉ እና በጣም በቆንጆ ስታንዳርድ እየተሰሩ ያሉ ናቸው። እኔና እናንተ ድሮ እንደምናውቀው ዓይነት ሰኞ ገብቶ አርብ የሚወጣበት፣ ዝም ብሎ የተለቀለቀ ሳንቃ ቤት አይደለም፤ በጣም ዘመናዊ መሠረተ-ልማት ነው እየተገነባ ያለው።

ክቡር ዶክተር ደሳለኝ ስለ መምህራንና ተማሪዎች ያነሱት ሐሳብ ትክክል ነው። ተማሪዎቻቸው እንዲያልፉ መምህራን የሚጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም። ነገር ግን እርሶም እንደሚያውቁት፣ በዘርፉ የነበረውን ስብራት ለመጠገን፣ ሪፎርም አድርጎ፣ መመሪያ አዘጋጅቶ ውጤት ለመሰብሰብ ጊዜ እንደሚወስድ በደንብ ይገነዘባሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የማይገባኝ የድሮ ፖለቲከኞች እሳቤ አለ። ባዮግራፊያቸውን ስታነቡ ወይም ስትሰሟቸው “በድሮው ክፍለ ሀገር ከነበረው ሃይስኩል እኔ ብቻ አንድ ሰው አልፌ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ” ይላሉ። አሁን ግን “እኔ ብቻ አልፌ ገባሁ” የሚባልበት ዘመን አልፏል። ብዙዎች በጋራ የሚያልፉበትን ዕድል መፍጠር አለብን። መሰረቱ ላይ ሳንሰራ ፍሬው ላይ ብቻ ብናስብ ዋጋ የለውም። ባለፉት ሰባት ዓመታት 35,000 ቅድመ-መደበኛ (ኪንደርጋርተን) ትምህርት ቤቶችን የገነባ መንግሥት፣ አሁን ደግሞ የ"መደመር ዩኒቨርሲቲ"ን በከፍተኛ ጥራት እየገነባ ይገኛል። ቀደም ሲል የነበሩ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎችን ብታዩ፣ ለምሳሌ ባህርዳርም ጅማም ብትሄዱ፣ 2000 እና 3000 ተማሪ የሚሸከሙ ባዶ ኮንዶሚኒየሞች ታያላችሁ። ምክንያቱም ድሮ ግንባታው የሚካሄደው ለኮንትራት ጥቅም እንጂ ለትምህርት ጥራት አልነበረም። አሁን ግን እኛ እየገነባን ያለነው ዩኒቨርሲቲ ከ6 እስከ 12 ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲያልቅ፣ በአፍሪካ ጭምር የዚያ ዓይነት ጥራት ያለው ግንባታ አይኖርም፤ ምክንያቱም ለልጆቻችን በጥራት ስለምንሠራው ነው።

በተለይ የኤአይ (AI) ጉዳይ ለሀገራችን እጅግ አስፈላጊ ነው። ታስታውሳላችሁ የዛሬ አምስት ስድስት ዓመት የኤአይ ተቋም እንፍጠር ስንል፣ አፍሪካ ውስጥ ይሄ አጀንዳ አልነበረም። አሁን ግን የወደፊቱ ጊዜ (Future) ኤአይ መሆኑን ሁሉም እየተናገረ ነው። ይህ መንግሥት ቀድሞ አውቆ በመሥራቱ፣ እስካሁን "መስብ"ን ጨምሮ በርካታ ውጤቶች አግኝተንበታል። የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ኩረጃን ለማስቀረት ቴክኖሎጂን ለመጠቀም እየተደረገ ያለው ሙከራ ተስፋ ሰጪ ነው። መምህራን፣ ወላጆችና ትምህርት ቤቶች አሁን እንደ ድሮው “እናስኮርጃለን” ብለው ከመዘናጋት ይልቅ፣ ልጆችን ማዘጋጀት ጀምረዋል። ማትሪክ ሲደርስ ልጆችና ቤተሰቦች ሲጨናነቁና ሲጠኑ ታያላችሁ። ይሄ አካሄድ ጠቃሚና የሚያዋጣ ነው።

አሁን ያሉን ልጆች እንደ እኛ ጊዜ አይደሉም፤ እሳት ናቸው! ያላቸው የግንዛቤ ደረጃ እጅግ ይደንቃል። በቅርቡ በአርባ ምንጭ ጉዞ ወቅት ገና ስምንት ዓመት ያልሞላው ልጄን ይዤው ሄጄ ነበር። በአባያ ሐይቅ ውስጥ ጉማሬና አዞዎችን ስናይ፣ አጠገባቸው ወፎች ነበሩ። መጀመሪያ ላይ “አይበሏቸውም እንዴ?” አለኝ። መልሶ ግን “ኦ ኖ ተወው፣ ወፎቹ ከአዞው ጥርስ ውስጥ ስጋ እንደሚያወጡ አውቃለሁ” አለኝ በስምንት ዓመቱ። እኔ ይሄንን ያወቅኩት በ38 ዓመቴ ነው። ስለዚህ የሚቀጥለው ትውልድ የሚያሰጋ አይደለም፤ እውቀታቸውን ከሀገር ፍቅርና ከጋራ ጥቅም ጋር ማያያዝ ብቻ ነው የሚጠበቅብን።

ሁለተኛው ነጥብ ሥራንና የሥራ ባህልን ይመለከታል። ወጣቶቻችን ከከተማ ወጥተው በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ መሥራት መልመድ አለባቸው። ሀገራችን ውስጥ በርካታ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም ሰራተኛ ማግኘት ግን ቀላል አይደለም። እዚህ ያለ የምክር ቤት አባል የቤት ሰራተኛ እጥረት ችግር የሌለበት የለም። በሌላ በኩል ደግሞ ወጣቱ “ሥራ የለም” ይላል። አዲስ አበባ ውስጥ ለቤት ሠራተኛ የሚከፈለው ክፍያ በአረቡ ዓለም ከሚከፈለው የሚበልጥበት ጊዜ አለ፤ ግን ሰው የለም። ሰው የሚፈልገው ብድግ ብሎ መኪና መንዳትና በአንድ ጊዜ ባለሀብት መሆን ነው እንጂ፣ ሁለት ሥራ መሥራት አይፈልግም። በአሜሪካ ያሉ ወንድሞቻችን ግን ቢል ለመክፈል ሁለት ሥራ እየሠሩ፣ ሁበር እየነዱ፣ በቀን 16 ሰዓት ይለፋሉ። የእኛ ቤተሰቦች ግን ዝም ብለው ተቀምጠው ፌስቡክ እያዩ “ሥራ የለም” ይላሉ። በሦስት ሺፍት እየሠራን ካልተጋገዝን ሕይወት እየከበደ መሄዱ አይቀሬ ነው።

ለምሳሌ በወንጪ ሐይቅ ላይ ያለችን አንዲት ጥንታዊት ታሪካዊት ቤተክርስቲያን ለማደስ ሰራተኛ አጥተን ከአዲስ አበባ ነው የወሰድነው። የቢሾፍቱን የአየር ማረፊያ (ኤርፖርት) ፕሮጀክት ብታዩት በሕይወታችሁ ከምታዩዋቸው አስደናቂ ሥራዎች አንዱ ነው። እዚያ ያለው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ቢሆንም ሠራተኛ ግን በቀላሉ አይገኝም። ይሄ በትክክል “የመንግሥት ሹሞች አሉ (Public Servant) ግን አገልግሎት (Service) የለም” እንደማለት ነው። ሥራና ሠራተኛን የምናገናኝበትን መንገድ ሁላችንም ልንተጋበት ይገባል።

ጤናን በተመለከተ፣ ዘንድሮ ለመድኃኒት ግዢ ብቻ መንግሥት 7 ቢሊዮን ብር አውጥቷል። በሀገር ውስጥ ይዘጋጅ የነበረው የመድኃኒት አቅም 4% የነበረ ሲሆን፣ አሁን ወደ 44-45% አሳድገነዋል። የአህሪ (AHRI) ላብራቶሪም ዋና ዓላማው የክትባት አቅምን የመቆጣጠርና የመደገፍ አቅም ለመፍጠር ነው። ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሕክምና መሣሪያዎችን እያስገባን ነው። በጳውሎስ ሆስፒታል ተጨማሪ የ1,000 አልጋ ሕንፃ ተገንብቷል። ነገር ግን የሀገሪቱ ፍላጎት ሰፊ በመሆኑ አሁንም ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል። በትጋታችን ምክንያት የዓለም የመድኃኒት ቁጥጥር ኤጀንሲ የኢትዮጵያን የብስለት ደረጃ (Maturity Level) ወደ 3 አሳድጎታል። ይህም ማለት ኢትዮጵያ የምታመርታቸው መድኃኒቶች ለውጭ ገበያ (Export) ደረጃ ተቀባይነት አላቸው ማለት ነው። በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ትኩረታችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታዩ ጸዱ ያሉ የሕክምና ተቋማትን መገንባት ይሆናል። በተጨማሪም የዲጂታል ቴክኖሎጂ ስኬታችን ትልቅ ነው፤ 5 ሚሊዮን ወጣቶችን በኮዲንግ ለማሰልጠን ያቀድነው ፕሮጀክት ተሳክቷል፣ "መስብ" አገልግሎትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከመቶ በላይ ቅርንጫፎችን ከፍቷል።

የውጭ ግንኙነትን በተመለከተ፣ ዓለም በአሁኑ ወቅት እጅግ ተለዋዋጭ፣ ውስብስብና ኢ-ተገማች ባህርይ ይዟል። በዚህ አውድ ውስጥ ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስከበር ፖሊሲያችን ተግባራዊ (Pragmatic) መሆን አለበት። እኛ የምንከተለው የሀገሬን ብልሃት ነው፦ “ውሃ ሲጠራ በአጭ ሰው ሲታወቅ በአት” ይላል። ውሃ ሲደፈርስ በጥንቃቄ ማየት፣ ሲጠራ ደግሞ የሚያስፈልገውን ነገር መጨለፍ ያስፈልጋል። የእኛ ዋና መርህ የኢትዮጵያን የውሳኔ ሉዓላዊነትና ስትራቴጂካዊ ነፃነት (Strategic Autonomy) ማስጠበቅ ነው። እኛ ሦስት “መ”ዎችን እንከተላለን፦ መቋቋም (ጠንካራ ሀገርና ተቋም መፍጠር)፣ መጠቀም (ፈተናዎችን ወደ ዕድል መቀየር)፣ እና መግራት (በሰው አጀንዳ ሳይሆን በራስ አጀንዳ መሪ መሆን)። በዓለም አቀፍ ግጭቶች ምክንያት “ኢትዮጵያ ትራባለች” የሚለውን ሟርት፣ እኛ ሌሊትና ቀን ሰርተን እራሳችንን በመመገብ አክሽፈነዋል።

በሌላ በኩል ጠላቶቻችንም ሳያውቁት ሦስት “መ”ዎችን ይከተላሉ፦ መካድ (የኢትዮጵያን ያለመንበርከክ ታሪክ መካድ)፣ መርሳት (የሀገራችንን ስትራቴጂካዊ ጥልቀትና የወጣት ኃይል መርሳት)፣ እና ምኞት (ያለፈበትና ያረጀ ስልት እስረኛ መሆን)። ትላንትና ሻዕቢያ፣ ወያኔና ሱዳን ተባብረው ደርግን እንደጣሉት፣ አሁንም ተባብረን የአሁኑን መንግሥት እንጥላለን የሚል ምኞት አላቸው። አሁን ግን ዘመኑ ተቀይሯል። በነዋሪነት 22 ማዞሪያና መገናኛ ሕንፃ ላይ ተቀምጠህ፣ ሀብት እያጣጣምክ ራስህን ለጦርነት ማዘጋጀት አብሮ አይሄድም። እኛ የምንፈልገው ሰላምና ልማት ነው። ለትግራይም ቢሆን ሰላም ከመጣ ፍላጎታችን እሱ ነው፤ እምቢ ያልንበት ምክንያት ጦርነት ትርፍ ስለሌለው ነው።

አንድ ነገር ግን በግልጽ ማወቅ አለባችሁ። የዛሬ 20 እና 30 ዓመት የነበሩ ሰዎች፣ አሁን እዚህ ፊት ለፊት የምታዩዋቸው መሪዎች ከወረዱ በኋላ ተመልሰው መጥተው “ኢትዮጵያን እንምራ” ካሉ፣ ሀገሪቱ አዲስ መሪ መፍጠር አልቻለችም ማለት ነው። 50 ዓመት ሙሉ ፓርቲ መርተህ የሚተካ ወጣት ካላፈራህ ኪሳራ ነው። TPLF 50 ዓመት ሙሉ ፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ ወጣቱን ትውልድ መተካት አለመቻሉ ትልቅ ኪሳራ ነው። አሁን ኒው ብለድ (አዲስ ደም) እና አዲስ አቅጣጫ የማይቀበል ኃይል የትም አይደርስም። የእኛ ትልቁ ምኞት እንደ ባህር ዳር፣ ጅማና አርባ ምንጭ ሁሉ በመቀሌም ወጣቶች በኮደርነት ሲሰለጥኑ ማየት ነው።

እባካችሁ “እኔ ሊቀመንበር ካልሆንኩ ወይም እኔ ካልመራሁት ሁሉ ነገር ይውደም” የሚለው እሳቤ መታረም አለበት። ይሄ በትግራይ ብቻ ሳይሆን በኦሮሚያም ይሠራል። “እኔ 40 እና 50 ዓመት ታግያለሁ፣ እኔ ከሌለሁ አይሆንም” የሚሉ አሉ። የኦነግን የትግል ታሪክ፣ ኦሮሞን ማቃቱንና ማደራጀቱን ማንም አይክድም፣ ክብር ይገባዋል። ጋሽ ዳውድ ኢብሳ ጀግና ናቸው፣ ላለፉት 40 ዓመታት በችግርና በመከራ ውስጥ ታግለዋል። ነገር ግን አሁን ያለው ዘመንና የሊደርሺፕ አቀራረብ ከድሮው ይለያል። አሁን የኤአይ (AI) ዘመን ነው። ኦፕሬቲንግ ሲስተሙ በጣም ፈጣን ነው። ይሄንን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከእንግዲህ በኋላ አዛውንቶችን ለምክር እንጂ ለፖሊሲ ምንጭነት አይፈልግም። ምክራቸውን እንሰማለን፣ ሲታመሙ እናክማለን፣ ሲሞቱ በክብር እንቀብራለን፤ ከዚያ ባለፈ ግን ፖሊሲ እንዲያመነጩ አንጠብቅም።

ታዲያ ኢትዮጵያ ምን ትሁን? ኢትዮጵያ እንደ ግራር ዛፍ ትሁን! የግራር ዛፍ ብዙ አስተማሪ ባህርያት አሉት፦

1. ሥሩ የጠለቀ ነው፦ የእኛም ሥራና አስተሳሰብ መጥለቅ አለበት (ልክ እንደ መደመር እሳቤ)።

2. ከፍ ብሎ ይበቅላል፦ ትናንሽና ያረጁ እሳቤዎች እንዳያደናቅፉን ከፍ ብለን መብቀል አለብን።

3. እሾሃማ ነውና ጋዛማ ሽታ አለው፦ ጠላት ሲመጣ እራሱን ለመከላከል እሾህ ያወጣል፣ ጋዛማ ሽታ ያፈልቃል። እኛም በጠላት እንዳንደፈር ራሳችንን የመከላከል አቅም መገንባት አለብን።

4. ችግርተኛ ጉንዳንን ያስጠጋል፣ ያበላል፦ እኛም በሰፈራችን ያሉ የአፍሪካ ወንድሞቻችን ሲቸገሩ ለማገዝ፣ ካለን አካፍለን ለመመገብ ሁሌም ዝግጁ ነን።

ኢትዮጵያ በዚህ መርህ ከሄደች ነው ለአፍሪካ ምሳሌ መሆን የምትችለው። ይህንን ለማድረግም ለሚቀጥሉት 25 ዓመታት ሀገሪቱ የምትመራበት በጣም ግልጽ ስትራቴጂ ነድፈናል። ይህ ስትራቴጂ ግልጽ ራዕይ (Vision) እና ዓላማ (Purpose) ያለው ሲሆን፣ 5 ስትራቴጂካዊ ዓላማዎች፣ 15 ሞዴሎች፣ 12 የኃይል ማዕዘናት (Power Vectors)፣ 9 ዲሲፕሊኖች እና 9 እርስ በርስ የተሳሰሩ አካላትን (Interdependencies) የያዘ ነው። በእርግጠኝነት እናሳካዋለን!

ቀሪውን ከ20 ደቂቃ የጤና ዕረፍት በኋላ ተመልሰን እንቀጥላለን። አመሰግናለሁ።

የተከበሩ አፈ ጉባኤ፤

በጥቂት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ለተነሱት ጥያቄዎች መጠነኛ ማብራሪያ አድርጌ፣ በጋራ ችግኝ ተክለን፣ ተስፋን ተክለን እንለያያለን።

 

ኢኮኖሚን በሚመለከት ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት፣ ዓለም በፈጣን ለውጥ ውስጥ፣ በብዙ ከፍታና በብዙ ዝቅታ እየተናወጠች ባለችበት በዚህ ዘመን ከፍተኛ ሀብት ይንቀሳቀሳል። ሰምተን የማናውቀው የሀብት ቁጥር ልክ ይነገራል፤ ከፍተኛ ፈጠራም የተገኘበት ዘመን ነው። ሆኖም ግን፣ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ትላልቅ ሀገራት የተሳተፉባቸው ዋና ዋና ግጭቶች በአለም ላይ ሲካሄዱ መቆየታቸው፣ በዓለም እድገት ላይ መጠነኛ ስብራትና ዝቅታ ፈጥሯል። የዓለም የንግድ ሥርዓት በመጠኑ ታውኳል፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም ቀንሷል። ይህም በንግድና በኢኮኖሚ እድገት ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።

 

የነዳጅ፣ የማዳበሪያና የሎጅስቲክስ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት በአንድ አካባቢ የተቀሰቀሰው ኢንፍሌሽን (የዋጋ ግሽበት) ወደ ብዙ ሀገራት ተዛምቷል። እኛም ጋር የራሱ የሆነ ጫና ያመጣ 'የገቢ ዕቃዎች ግሽበት' (Imported Inflation) አስከትሏል፤ ምክንያቱም በምናስገባቸው ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ በመፈጠሩ ተያያዥ ችግሮች መጥተዋል።

 

ነገር ግን ቀደም ሲል በአንዳንዶቻችሁ እንደተነሳው፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ ያካሄደችው የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ እንደ ፓርቲ ወይም እንደ መንግሥት ሳይሆን ሀገሩን እንደሚወድ ዜጋ በጥልቀት ለተመለከተው ሰው ትልቅ ትርጉም አለው። በርካታ ሪፎርሞች በሴክተር ደረጃ የተካሄዱ ቢሆንም፣ የማክሮ ኢኮኖሚክስ ስብራቶቻችን እንዲቃኑ፣ ኢትዮጵያ በጽናት (Resilient) እንድትቀጥልና እድገቷ እንዲረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ማንኛውም ኢኮኖሚስት ከምንም ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ በጥሞና ማየት ከቻለ፣ ይህ ከመንግሥትነት ባሻገር የሀገር ብልጽግናንና ለውጥን ታሳቢ ያደረገ፣ ትልቅ ድፍረት የተሞላበትና በደንብ የተመራ ጀኑን ሪፎርም እንደነበረ ይገነዘባል። በዚህም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከነበረበት አረንቋና ችግር በመጠኑም ቢሆን አገግሞ ተስፋ እንዲሰንቅ ዕድል አግኝቷል። ይህንን ሪፎርም በጥንቃቄ ማየትና ትምህርት መውሰድ አስፈላጊ ይመስለኛል።

 

በሴክተር ደረጃ ብናይ፣ ግብርና አንዱ ዋና ምሰሶአችን ቢሆንም ኢኮኖሚያችን ዳይቨርሲፋይ መሆን (መክበብ/መተመን) አለበት፤ በአንድ ሴክተር ላይ ብቻ ተንተርሰን ከምናስበው ልማት ልንደርስ አንችልም በሚል እምነት በግብርናው ዘርፍ በክላስተር ማሽን ማስፋፋት፣ መሬትና ምርጥ ዘር ማቅረብ፣ እንዲሁም የርጭትና መስኖ ግድቦችን መገንባት ላይ የሰራነው ስራ በጣም ትልቅ ውጤት አስገኝቷል። ዘንድሮ ኢትዮጵያ 29 ሚሊዮን ሄክታር መሬት አርሳ፣ ወደ 1.3 ቢሊዮን ኩንታል ምርት ሰብስባለች።

 

በሌማት ትሩፋት የጀመርነው ኢኒሼቲቭም በጣም አስደናቂ ውጤት እያስገኘ ይገኛል። ለምሳሌ በአቮካዶ ምርት በአፍሪካ ሁለተኛው ኤክስፖርተር በመሆን በጣም ከፍተኛ ገቢ አግኝተንበታል። ስንጀምረው አቮካዶ ለኤክስፖርት ይበቃል ተብሎ እንኳን የማይታሰብ ነበር፤ አሁን ግን የውጭ ምንዛሬ እያመጣ ነው። ከዚህ አጠቃላይ ለውጥ ውጪ በተለየ አካባቢ ስንመለከት፣ ለብዙ ጊዜ በድርቅና በረሃብ የምናውቃቸው በሶማሌና በአፋር ክልሎች ሰፋፊ የስንዴ ማሳዎችና እርሻዎች እየታዩበት ይገኛል። ይህም በእርሻ ላይ አበክረን ብንሰራ ውጤት ማግኘት እንደምንችል በተግባር አስመስክሯል። ለረጅም ጊዜ ቆመው የነበሩና አዳዲስ የጨረስናቸው በርካታ ግድቦች ተደምረው፣ የግብርናው ሴክተር በዚህ ዓመት 7.7% እድገት እንደሚያስመዘግብ ከአመላካቾች መታየት ችሏል። (ርግጥ ነው፣ አጠቃላይ እድገቱ ተደምሮ የሚታወቀው በመስከረም ወር ቢሆንም የግብርናው ዘርፍ ብቻ 7.7% እድገት ይጠበቃል)።

 

ቅድም እንዳነሳሁት፣ ኢኮኖሚውን ዳይቨርሲፋይ ለማድረግ ትኩረት ካገኙት ዘርፎች አንዱና ዋናው የኢንዱስትሪ ሴክተር ነው። አዲሶቹን ፋብሪካዎች እንተዋቸውና፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከለውጡ በፊት የነበሩት ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸው ከ47 ፐርሰንት በታች ነበር፤ ማለትም ግማሽ ያህሉ አያመርቱም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ፋይናንስ፣ መሬት ወይም የኢነርጂ አቅርቦት ሊሆን ይችላል። እኛ ኮሚቴ አቋቁመን፣ እያንዳንዱን ኢንዱስትሪ በአካል ጎብኝተን ችግሮቻቸውን ለመፍታት ባደረግነው ጥረት፣ ዛሬ ቀድሞ የነበሩት ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸው ወደ 67 ፐርሰንት ከፍ ብሏል። ይህም ከ40 ፐርሰንት በላይ መሻሻል ማሳየታቸውን የሚያመለክት ትልቅ እመርታ ነው። ይህ እያንዳንዱን ፋብሪካ ይነካል፤ እዛ ውስጥ አዲስ ስራ ይቀጠራል፣ ቢዝነስና ሀብት ይፈጠራል ማለት ነው።

 

ከዚያ በተጨማሪ፣ ከኮምቦልቻ፣ መቐለና ሐዋሳ ውጪ ከአስር ያላነሱ አዳዲስ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የገነባን፣ የግሉን ዘርፍና የውጭ ኢንቨስተሮችን ያስገባን እኛ ነን። ሐዋሳን ጨምሮ በጥቂት ኢንቨስተሮች ተይዘው የነበሩትን ፓርኮች ከ80% በላይ ኢንቨስተር እንዲመጣባቸው አድርገናል። ስለዚህ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ እድገት አለው፤ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ሽግሽግም መታየት ጀምሯል። ለምሳሌ በሚቀጥለው ዓመት ከኢንዱስትሪ ኤክስፖርት ብቻ 1 ቢሊዮን ዶላር ይጠበቃል። ቀደም ሲል ስለ 100 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ያወራ የነበረ ዘርፍ አሁን 1 ቢሊዮን ዶላር ይጠበቅበታል ማለት ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸውን ያሳያል። ነገር ግን ኢንዱስትሪ በባህሪው በሐምሌና ነሐሴ ትራክተር ገዝተን አርሰን፣ በጥቅምትና ህዳር የምንሰበስበው (Harvest የምናደርገው) ፈጣን ዘርፍ አይደለም፤ ጊዜ ይፈልጋል።

 

በሌላ በኩል፣ 'የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ እንተካ' (Import Substitution) ብለን በወሰድነው አቋም፣ በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከውጭ ታስገባቸው ከነበሩ የኢንዱስትሪ ምርቶች ውስጥ የ5 ቢሊዮን ዶላር ምርት በሀገር ውስጥ ማምረት ችላለች። ለምሳሌ ሴራሚክስን ብንወስድ፣ 'ድንጋይ ከውጭ አንሸምትም' ብለን ጣልቃ በመግባት (Intervene በማድረግ) አንድ ሳይሆን ሁለት ትላልቅ ፋብሪካዎች አልቀዋል፤ አንዱ ተመርቋል፣ ሌላኛው ደግሞ በቅርቡ ይመረቃል። በሲሚንቶ፣ በመስታወትና በብረት ላይም ሰፋፊ ስራዎች ተሰርተዋል። ካልዘነጋችሁት በቀር፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የሶላር ምርቶችን ወደ ውጭ መላክ (Solar Export) የሚባል ነገር አታውቅም ነበር፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግን የት እንደደረስን ታውቃላችሁ። እናም በኢንዱስትሪው ላይ ይበል የሚያሰኝና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ነው ያለው።

 

በኢንዱስትሪ ሴክተር ውስጥ የሚታየውንና እራሱን ችሎ መሪ የሆነውን የማዕድን ዘርፍ ብንወስድ፣ በዚህ ዓመት ብቻ የ24 ፐርሰንት እድገት አሳይቷል። ማኑፋክቸሪንግ 20.3% አድጓል። በሲሚንቶ ምርት ደግሞ የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከመጣና የነበሩትን አቅሞች ካሳደግን በኋላ በዚህ ዓመት የ16% የምርት እድገት አለ። በኢነርጂ አጠቃቀም ረገድ በዚህ ሴክተር ብቻ የ23% እድገት ታይቷል። አሁን ዋናው ጥያቄያችን መሆን ያለበት 'አጠቃላይ የመጣውን ውጤት እንዴት እናስጠብቀው? የኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽኑ ግብርናን እንዲተካና ሰርቪስ ሴክተሩን የመገዳደር አቅም እንዲኖረው እንዴት እናድርገው?' የሚለው እንጂ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተወሰደው እርምጃ ተጨባጭ እድገት ማምጣቱ ምንም የሚካድ ጉዳይ አይደለም። በዚህ ዓመት በአጠቃላይ ከኢንዱስትሪ ዘርፍ 12.7% እድገት ይጠበቃል። ይህ እድገት ዝም ብሎ ሊመጣ አይችልም፤ በአንድ ንዑስ ዘርፍ (Sub-sector) ላይ 12.7 ፐርሰንት እድገት መመዝገቡ ለረጅም ጊዜ የተሰራውን ስራ ያሳያል።

 

የአገልግሎት (Service) ዘርፍን ብናይ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከለውጡ በፊት ከነበረው የማጓጓዝ አቅም በትንሹ የሶስት እጥፍ እድገት አሳይቷል። በዚህ ዓመት 17 ሚሊዮን ያህል የውጭ መንገደኞችን እንዲሁም 4 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ መንገደኞችን—በድምሩ 21 ሚሊዮን ገደማ ሰዎችን አጓጉዟል። ይህም ያስገኘው ከፍተኛ ሀብት አለ።

 

ዲጂታላይዜሽንን በሚመለከት፣ በንግድ፣ በፋይናንስና በትራንስፖርት ዘርፎች ትልቅ ለውጥ መጥቷል። በተለይም በኩነቶች (Events) ረገድ፣ በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ውስጥ ከመቶ በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች (International Summits) ተካሂደዋል ሲባል እንዴት ነው የምናየው? ይህ በጣም ብዙ፣ ወደ 100,000 የሚጠጋ ሰው የተስተናገደበት ነው። ከተማዋን ያጨናነቀው የእኛ ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ በየጊዜው ኮንፈረንሶችና ሰሚቶች ስላሉ ነው። ይህ ተደማምሮ የአገልግሎት ዘርፉ (Service Sector) 9.8% እድገት እንደሚያመጣ ይጠበቃል።

 

አጠቃላይ የፍላጎትና የአቅርቦት አዝማሚያዎች ተጠቃለው በጥልቀት የሚታወቁት መስከረም ገደማ ቢሆንም፣ አሁን ያሉት ማሳያዎች የኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት 10.2% ወይም 10.3% ገደማ ሊሆን እንደሚችል ያመለክታሉ። ክቡራትና ክቡራን፣ ይህ በአፍሪካ ትልቁ እድገት ነው! በሪፎርሙ ወቅት ለኢትዮጵያ ህዝብ 'አስተማማኝ እድገት እናመጣለን' ብለን ቃል ገብተን ነበር፤ ይመስገን፣ ተሳካልን! ተሳካልን ሲባል ግን ሩጫችን አለቀ ማለት አይደለም። የሩጫችን አቅጣጫ ትክክለኛ መሆኑን አረጋገጥን ማለት እንጂ ገና ብዙ ብዙ ስራ ይጠብቀናል።

 

እስኪ ትንሽ ገባ ብለን እንይ፤ ቅድም አንዳንዶቻችሁም አንስታችሁታል። የዘንድሮው የኢትዮጵያ የሸቀጦች ኤክስፖርት ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆኖ መጠነኛ ጭማሪ አሳይቷል። ዛሬ በተቻለ መጠን የአንዳንድ ወገኖችን ስም መጥቀስ አልፈልግም፣ ነገር ግን ኤክስፖርቱን ያነሱት ጉዳይ ላይ ለግንዛቤ ያህል፤ 11 ቢሊዮን ዶላር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ክቡር ዶክተር ደሳለኝ በኋላ ዳታውን እንዲያዩት እጋብዛለሁ። ከ1984 እስከ 2000 ዓመተ ምህረት ባሉት 17 ዓመታት ውስጥ፣ ኢትዮጵያን የሚያክል ሀገር በጥቅሉ ኤክስፖርት አድርጎ ያገኘው 11 ቢሊዮን ዶላር ነው። የ17 ዓመቱን ድምር ምርት በአንድ ዓመት ማምጣት እድገት ካልሆነ ታዲያ እድገት ምንድን ነው? ከሰማንያ እስከ ሁለት ሺህ ዓ.ም ያለውን የኢትዮጵያ ኤክስፖርት ብትደምሩት 11 ቢሊዮን ዶላር ነው። ይህንን የ17 ዓመት ሙሉ ልፋት ዘንድሮ በአንድ ዓመት አመጣነው። ይህ የግለሰብ ወይም የቤተሰብ ድል አይደለም፤ የመላው ኢትዮጵያውያን ትልቅ ድል ነው።

 

የኢትዮጵያ አቅም በዚህ ያበቃል ወይ? አይደለም፤ በብዙ እጥፍ ማደግ አለበት። ነገር ግን ከነበርንበት አንጻር በፍጹም ሊናቅ አይችልም። እኔ በዚህ ዓመት ለእናንተና ለካቢኔው ባቀረብኩት እቅድ ላይ '9.8 ቢሊዮን ብንደርስ ትልቅ ነገር ነው' ያልነው፤ አፈጻጸሙ ግን ከእቅዳችን በእጅጉ የላቀ ሆኗል። የ17 ዓመት ኤክስፖርት በአንድ ዓመት መምጣቱ ትልቅ ስኬት ቢሆንም፣ በሚቀጥለው ዓመት ከዚህ በላይ እያደገና እየሰፋ መሄድ ይኖርበታል።

 

በተጨማሪም በአገልግሎት ዘርፍ 9.5 ቢሊዮን ዶላር አግኝተናል። በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FDI)፣ ቃል የተገባውን ትቼ በተግባር የገባውን ስናይ 4 ቢሊዮን ዶላር ገደማ አግኝተናል። ሬሚታንስ (የዲያስፖራ ሐዋላ) ወደ 7.9 ቢሊዮን—ለስምንት ቢሊዮን ጥቂት የቀረው—አግኝተናል። ሌሎች እርዳታና ብድሮችን ጨምሮ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገብቷል። በድምሩ በዚህ ዓመት 38 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የውጭ ካፒታል ወደ ሀገር ውስጥ ፈስሷል።

 

በዚህ ውስጥ ኤክስፖርቱ 11 ቢሊዮን ዶላር መሆኑ የብዙ ዓመታት ክምር ውጤት ነው ለሚለው፣ ጥቂት ምሳሌዎችን አንድ በአንድ እንይ። ለምሳሌ ቡናን እንውሰድ፤ ኢትዮጵያ የኮፊያ አረቢካ መገኛ ናት፣ በማንኛውም ዘመን ቡና ወደ ውጭ ትልክ ነበር። እግረ መንገዱን የ'አረንጓዴ አሻራ' (Green Legacy) ጥቅሙ እንዲገባችሁ፤ ኢትዮጵያ ለ17 ዓመታት ሙሉ ቡና ወደ ውጭ ሀገር ልካ ያገኘችው አጠቃላይ የዶላር መጠን 3.3 ቢሊዮን ዶላር ነበር። ዘንድሮስ? በአንድ ዓመት ብቻ 3.1 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች! ይህ ቡና ነው፤ ካልተከልን፣ ካልተንከባከብን፣ ካልቀጠፍን፣ ካላጠብን፣ ካላሸግንና ካላጓጓዝን ይህ ውጤት ሊመጣ አይችልም። በነገራችን ላይ የቡና የሀገር ውስጥ ፍጆታ (Consumption) ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ከነበረው አሁን በጣም ጨምሯል፤ ህዝብ እየበዛና ፍላጎት እያደገ መጥቷል። የሀገር ውስጥ ፍላጎቱን አሟልተን፣ በዓለም ደረጃ ከብራዚልና ከኮሎምቢያ ቀጥሎ ሶስተኛው ትልቁ የቡና ኤክስፖርተር በመሆን 3.1 ቢሊዮን ዶላር አስገብተናል። ይህ በአፍሪካ አንደኛ፣ በአለምም ሶስተኛ ያደርገናል። ይህ የረጅም ዓመታት ክምር ውጤት ሳይሆን ሪፎርሙ ያመጣው ድል ነው።

 

ወደ ወርቅ ምርት ብንሄድ፣ (17 ዓመት ካልኩ ማነሱ ስለማይቀር) በ27 ዓመታት ውስጥ—ማለትም ከ1980 እስከ 2011 ዓ.ም—ኢትዮጵያ ወርቅ ወደ ውጭ ልካ ያገኘችው 3.7 ቢሊዮን ዶላር ነበር። በዚህ በአንድ ዓመት ብቻ ግን ኦልሞስት 5.5 ቢሊዮን ዶላር ገብቷል! ይህ ትልቅ እድገት ነው። የአንድ ዓመት አፈጻጸም የ27 ዓመቱን ድምር ሲበልጥ እድገት ካልተባለ፣ ወደፊትም ወደ ከፍታ ለመሻት እንቸገራለን። ይህ ዝም ብሎ ቁጥር ሳይሆን የሚጨበጥ፣ የሚዳሰስና የሚታይ እድገት ነው።

 

የውጭ ምንዛሬ ክምችታችንን (Reserve) ብንመለከት፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረበት የ20 እጥፍ በላይ አድጓል። ሪዘርቫችን ከ20 እጥፍ በላይ አደገ ማለት የኢትዮጵያ የመቋቋም አቅምና የጽናት (Resilience) አቅሟ ጨምሯል ማለት ነው። አሁን ያለን ክምችት ኢትዮጵያ ሀገር ሆና ከተፈጠረች ጀምሮ ከነበራት ትልቁ የሪዘርቭ መጠን በእጥፍ ይበልጣል። ይህ ትልቅ ስኬት ነው። እኛ ወደ ሥልጣን ስንመጣ ይህ ሀብት ቢኖር ኖሮ አንቸገርም ነበር፤ ማክሮ ኢኮኖሚክ ኢምባላንስ (መዛባት) ተፈጥሮ ስለነበር ነው ሪፎርም ለማድረግ የተገደድነው። ይህ የመላው ኢትዮጵያውያን ድል በመሆኑ በዚያው ልክ መታየቱ ጠቃሚ ነው።

 

ገቢስ? የገቢ ሪፎርም አካሂደን፣ ዲጂታላይዜሽን ሰርተን፣ 'ኢንፎርማል' (ህገ-ወጥ/ያልተመዘገቡ) ቢዝነሶች ወደ ሕጋዊ መስመር መግባት አለባቸው ብለን በሰራነው ስራ 43,000 ኢንፎርማል የነበሩ ቢዝነሶች ግብር መክፈል ጀምረዋል። የመጣውን ለውጥ ማየት ከፈለጋችሁ፤ ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያ የሰበሰበችው አጠቃላይ ገቢ 1 ትሪሊዮን ብር ገደማ ነበር፤ ዘንድሮ ግን 1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል። የ27 ዓመቱን ገቢ መብለጥ ብቻ ሳይሆን የ150% ጭማሪ አለው ማለት ነው። 'ይህ ገንዘብ ድሮ ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረም ወይ?' ካላችሁኝ፣ ከየትም አልመጣም፤ እዚሁ ነበር። ነገር ግን የሀገሪቱ ኢንፎርማል ኢኮኖሚ ከፎርማል (ሕጋዊ) ኢኮኖሚው ይበልጥ ግዙፍ ስለነበር፣ ሥርዓት ባለው መንገድ ገቢ ማስገባት የተለመደ ተግባር አልነበረም።

 

እግረ መንገዴን ለኢትዮጵያ ነጋዴዎች መልእክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፤ በጣም ብዙ ብርቱ ጥረት የሚያደርጉ ነጋዴዎች እንዳሉ ሆነው፣ በአለም ላይ ከውጭ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ 100% የትርፍ ህዳግ (Profit Margin) መያዝ የተለመደ አይደለም። የእኛ ነጋዴዎች ግን አስቡበት፤ በብዙ ምርቶች ላይ መቶ ፐርሰንት ትርፍ ይይዛሉ። ለምሳሌ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን (EV Cars) ብንወስድ፣ ከ3.5 ሚሊዮን እስከ 4 ሚሊዮን ብር ባለው ወጪ የሚገባን አንድ አይነት መኪና እዚህ ገበያ ላይ በከፍተኛ ዋጋ ይሸጣሉ፤ ድርድሩም 'ደረሰኝ ትቀበላለህ ወይስ አትቀበልም? ፎርማል ነው ወይስ አይደለም?' በሚል ነው የሚካሄደው። መኪና የምታስገቡ ሰዎች፣ የኤሌክትሪክ መኪና ማስገባታችሁን የምንደግፈው ቢሆንም፣ በምናደርገው ስውር ክትትልና ሱፐርቪዥን ከሚታየው ገበያ ውጪ የሚደራደር መኪና መሸጫ ካለ እንዘጋዋለን። ወደዛ እርምጃ ከመሄዳችን በፊት፣ ማትረፍና መጠቀም መብታችሁ ቢሆንም የትርፍ ህዳጋችሁ ትክክለኛና ምክንያታዊ ይሁን። በአንድ ጊዜ ብቻችሁን ለመበልጸግ የሚደረግ ጥረት በጥቅሉ ጎጂ እንጂ ጠቃሚ አይደለም፤ ዘላቂ (Sustainable) የሆነ ቢዝነስ ነው መፈጠር ያለበት። ነጋዴዎች ይህንን ከግምት ውስጥ ካስገቡ ጥሩ ይሆናል። አሁን 'በቂ ገቢ ሰበሰብን ወይ?' ከተባለ፣ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ኢንፎርማል ኢኮኖሚ አሁንም ግዙፍ ነው። የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ በመሆኑ ኮንትሮባንዱንና ኢንፎርማል ዘርፉን መስመር ማስያዝ ያስፈልጋል፤ ይህ የሁላችንም የጋራ ጥረት መሆን አለበት።

 

የበጀት ጉድለትን (Deficit) በሚመለከት፣ የኢትዮጵያ የዚህ ዓመት የውጭ በጀት ጉድለታችን 218 ቢሊዮን ገደማ ወይም ከ0.2% በታች ነበር። ይህ በየትኛውም መመዘኛ በጣም ዝቅተኛ የሚባል ጉድለት ነው። ያንን ጉድለት የሞላንበት መንገድ ደግሞ፣ ከማዕከላዊ ባንክ (National Bank) እየተበደርን ሳይሆን፣ የግምጃ ቤት ሰነድ (Treasury Bills) ሽያጭና ሌሎች ጤናማ ሶርሶችን በመጠቀም ነው። ይህ በጣም ጤናማ የሚባል የበጀት ጉድለት ማሟያ መንገድ ነው። ገቢያችንን አሳደግን እንጂ ወጪያችንን አይታችሁ ከሆነ እናንተ ካፀደቃችሁት በጀት ውስጥ የተወሰነውን ይዘን (ሳንነካው)፣ ከዚያ ባነሰ ወጪ ነው ዓመቱን ለመጨረስ ጥረት ያደረግነው። ስለዚህ የግምጃ ቤት ግብይቱ በጣም ጠቃሚና አስፈላጊ የነበረ ጤናማ የበጀት ማሟያ መንገድ ነው። በነገራችን ላይ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በአምናና በዘንድሮው ዓመት፣ የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስቴር ከማዕከላዊ ባንክ አንድም ሳንቲም ሳይበደር ዓመቱን አጠናቋል። የኢኮኖሚውን ጤናማነት ማሳያ ይሄ ነው፤ በዚህ ዘርፍ ያሉ የዓለም አቀፍ ተቋማት በሁሉም ጉዳይ ባይስማሙም፣ በእነዚህ ስራዎቻችን ግን በአንድ ድምፅ እያደነቁና እያመሰገኑ ስለሆነ፣ ሌሎቻችንም ትችታችን እንደተጠበቀ ሆኖ እንደዚህ አይነት ጠንካራ ጎኖችን ማየት ጠቃሚ ይመስለኛል።

 

ከሀገር ውስጥና ውጭ እዳ ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ፤ አንዱ ልንመሰገንበት የሚገባው አንኳር ስራ የኢትዮጵያን እዳ በሚመለከት የወሰድናቸው ውሳኔዎች ናቸው። 'እዳው ችግር አለበት፣ አመጣጡም ግፍ ነው' ብለን የወሰድናቸውን እርምጃዎች የተከበረው ምክር ቤት በከፍተኛ አክብሮት ሊያየው ይገባል። ለምሳሌ፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት አንድም ዶላር የንግድ ብድር (Commercial Loan) አልተበደርንም። ይህ እንዴት ቀለል ተደርጎ ይታያል? ብዙ የአፍሪካ ሀገራት እኮ ኮሜርሻል ሎን ተበድረው ነው ደሞዝ የሚከፍሉት። እኛ ግን 'ለልማትም ቢሆን የንግድ ብድር አያስፈልገንም' የሚል ጠንካራ ውሳኔ ነው የወሰድነው። ታስታውሳላችሁ፣ የዛሬ ዓመት አካባቢ 'ኢትዮጵያ እዳ መክፈል አቅቷት ዲፎልት አርጋለች' ተብሎ ስለ ዩሮ ቦንድ (Eurobond) ጉዳይ ሲወራ ነበር፤ ያኔም ተናግሬያለሁ፣ ኢትዮጵያ መክፈል አቅቷት ሳይሆን እነዚያ እዳዎች በድርድር መልክ መያዝ አለባቸው በሚል እምነት እንደሆነ ገልጬላችኋለሁ። አበዳሪዎቻችንንም እናመሰግናለን፤ ተሳክቶልን የዩሮ ቦንድን ጨምሮ ከብዙ አበዳሪዎቻችን ጋር ተስማምተናል።

 

ምን ተስማማን? የእዳ ሽግሽግ (Debt Restructuring) ማለት ምን ማለት ነው? የኢትዮጵያ እዳ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ (GDP) ጋር ሲነጻጸር ከ50 ፐርሰንት በላይ ስለነበረ፣ ሀገሪቱ 'ቀይ መስመር' ውስጥ ገብታለች፣ ተጨማሪ ብድር ብትወስድ ለመክፈል ትቸገራለች የሚል ነበር ክርክሩ። አሁን በሰራነው ሪፎርም ግን፣ በአፍሪካ ውስጥ ጤናማና ግዙፍ ከተባሉ ኢኮኖሚዎች አንዱ የእኛ ሆኗል። ይህም ማለት የኢትዮጵያ ብድር ከጂዲፒ አንጻር ከ45 ፐርሰንት በታች እንዲወርድ ተደርጎ፣ ሀገሪቱ በራሷ በምታመነጨው ሀብት ልትከፍል እንደምትችል በትላልቅ የፋይናንስ ተቋማት ታምኖበታል ማለት ነው። እኛ ያለን እዳ፣ በአፍሪካ አንደኛ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ከሚባሉ ህዝባዊ ኢኮኖሚዎች እዳ ጋር ሲነጻጸር አይነካካም፤ የእነሱ እዳ ከእኛ በሶስትና አራት እጥፍ ይበልጣል፣ አሁንም ቀይ መስመር ውስጥ ናቸው። እኛ ግን እዳችንን አውርደነዋል።

 

ለምን? የእዳ ሽግሽጉ የንግድ (Commercial) እና የዕርዳታ/የማቅለያ (Concessional) ብድርን ልዩነት ያገናዘበ በመሆኑ ነው። በግልጽ ለመረዳት፣ ኮሜርሻል ብድር ማለት 'አራጣ' እንደማለት ነው፤ ህጋዊ ቢሆንም በአጭር ጊዜ (በ3 እና 4 ዓመት) ውስጥ እንድትከፍል የሚጠየቅበት፣ ወለዱም ከ7 እስከ 8 ፐርሰንት የሆነ ነው። ኮንሴሽናል (Concessional) ሲሆን ግን፣ ክፍያው እስከ 30 ዓመት ይራዘማል፣ ወለዱ 1 ፐርሰንት አካባቢ ነው፣ የእፎይታ ጊዜውም (Grace Period) 10 ዓመት ይሆናል። ይህም ማለት አንድ ሀገር ተበድራ ኢንቨስት አድርጋ ትርፍ ማግኘት እስክትጀምር ድረስ 'እዳ ክፈይ' አትባልም። የንግድ ብድርን ጉዳት ለመረዳት የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ፕሮጀክትን መመልከት ይቻላል፤ ከጅቡቲ የዘረጋነው ባቡር ስራው በቅጡ ሳያልቅና ለሰራተኞች ደሞዝ መክፈል ሳይጀምር፣ አበዳሪዎቹ 'ብራችንን አምጡ' አሉ። ለሰራተኞች የሚከፈለውን ትተን ስራውን ማስቀጠል በማንችልበት ሰዓት ላይ ጫና ፈጠሩ። ብድሩ ኮንሴሽናል ቢሆን ኖሮ ግን የ15፣ 20 ወይም 30 ዓመት ረዘም ያለ ጊዜ ስለሚሰጥ፣ በዚያ ጊዜ ውስጥ ፕሮጀክቱን አጠናቆና ትርፋማ ሆኖ እዳን በአግባቡ መክፈል ይቻል ነበር። ስለዚህ ባለፉት ስምንት ዓመታት አንድም ዶላር የኮሜርሻል ብድር ባለመውሰዳችን የገንዘብ ሚኒስቴርና የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድኑ ትልቅ ድል አስመዝግበዋል። የሀገር ውስጥ ብድር አለ፣ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ ምን ችግር አለው? ያለ ብድር መስራት አለማወቅ ነው። ብድር ለልማት አስፈላጊ ነው፤ የግሉ ዘርፍም ቢሆን ቢዝነሱን የሚያሰፋውና ሪስክ የሚወስደው በብድር ነው። 100 ብር እያለው መቶውንም ከኪሱ አውጥቶ ኢንቨስት ከሚያደርግ፣ 70 ከራሱ 70 ከባንክ ወስዶ ቢሰራ ነውር አይደለም፤ ትክክለኛው አካሄድ (Approach) እሱ ነው። አደገኛ የሚሆነው ብድሩን የሚከፍልበት ጊዜና ሁኔታ (Term) ነው፤ ብድር አገኘሁ ተብሎ ዝም ብሎ መውሰድ ሳይሆን ለመክፈል የሚያስችል ቁመና መፍጠሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ስለዚህ የተከበረው ምክር ቤት በእነዚህ የእዳ ማቅለልና የኮመን ፍሬምወርክ (Common Framework) ስምምነቶች ላይ ሊኮራ ይገባል። ከጂ20 ሀገራትና ከዩሮ ቦንድ ባለቤቶች ጋር የተፈራረምናቸው ስምምነቶች ትልቅ ድሎች በመሆናቸው፣ የማክሮ ቡድኑን ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ።

 

ፋይናንስን በሚመለከት፣ የህዝብ ቁጠባ ተሻሽሎ ወደ 4.5 ትሪሊዮን ብር ደርሷል። አጠቃላይ ብድር ደግሞ ወደ 2.6 ትሪሊዮን ብር ደርሷል። የዘንድሮው ብድር ብቻ 1 ትሪሊዮን ብር ገደማ የሚጠጋ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከ90% በላይ የሚሆነው ለግሉ ዘርፍ (Private Sector) የተሰጠ ነው። ይህ በጣም ትልቅ እመርታ ነው። የተመለሰ ብድርን ስናይም የ14% እድገት አለ። የፋይናንስ ሴክተሩ፣ በተለይ አዲሱ የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ ከመጣ በኋላ፣ በትይዩ ገበያ (Parallel Market/ጥቁር ገበያ) እና በሕጋዊው ገበያ መካከል ያለው ልዩነት ከ100 ፐርሰንት ወደ 12 ፐርሰንት ዝቅ ማለቱ ትልቅ እመርታ ነው። ያ አሁንም ተጨማሪ ስራ ይፈልጋል፤ ከዚያም በላይ መጠንከር አለበት። ዘንድሮ ማዕከላዊ ባንክ ወደ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ለገበያ አቅርቧል፤ ያንን ሚዛናዊ (Balance) ለማድረግና የገንዘብ ግብይቱን ለማረጋጋት ተጨማሪ ስራዎች ይሰራሉ። በአጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፍ ዲጂታላይዜሽኑ ያመጣው ኢምፓክት፣ የሀገሪቱን የገንዘብ እንቅስቃሴ ከቢሊዮኖች ወደ ትሪሊዮኖች የሚያወራ ሴክተር አድርጎታል፤ ይህ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

 

የስራ ዕድል ፈጠራን በሚመለከት፣ በጣም ጥሩ ስኬት ያየንበት ዓመት ይህ ዓመት ነው። በዚህ ዓመት በሀገር ውስጥ 3.9 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል። በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ደግሞ ከ600 ሺህ በላይ ሰዎች ስራ አግኝተዋል፤ ይህ ዝም ብሎ ስራ ሳይሆን የክህሎትና ከፊል ክህሎት (Skilled and Semi-skilled) ያላቸውን ፕሮፌሽናሎችን ጭምር ያካተተ ነው። በቅርቡ በጀመርነው የሪሞት (Remote/የርቀት ዲጂታል) ስራ ደግሞ 40 ሺህ ሰዎች እዚሁ ሆነው ስራ አግኝተዋል። በድምሩ ከ5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ስራ ያስገኘ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ነበረ። ከዚህ ውስጥ አንደኛውና ዋናው ስራ ፈጣሪ ዘርፍ ግብርና ሲሆን፣ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ይዟል። ሁለተኛው የአገልግሎት ዘርፍ ሲሆን፣ በንግድ፣ በዲጂታላይዜሽንና በከተማ ውስጥ በሚሰሩ ስራዎች ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ስራ አግኝተዋል። ሶስተኛው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ሲሆን ከ900 ሺህ በላይ ስራ ፈጥሯል። በአጠቃላይ በሀገር ውስጥ የስራ ዕድል ፈጠራ ከአምናው የ13 ፐርሰንት፣ የውጭ ስምሪቱ ደግሞ የ27 ፐርሰንት እድገት አሳይቷል። 5 ሚሊዮን ህዝብ ስራ ማስያዝ የሚችልና በፍጥነት ማደግ የሚችል ኢኮኖሚ ትልቅ ስኬት ቢሆንም፣ ዳውንሳይድ (ክፍተት) አይኖረውም ማለት አይደለም፤ እሱን እያየን ማስተካከል አስፈላጊ ይሆናል።

 

የዋጋ መረጋጋትን በሚመለከት የተነሱት ጥያቄዎች ከሞላ ጎደል ገንቢና ጠቃሚ ናቸው። ጉዳዩን በሁለት መንገድ ማየት ጥሩ ነው፤ አንደኛው ኢንፍሌሽን (የዋጋ ግሽበት) ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የኑሮ ውድነት (Living Cost) ነው፤ አንዳንዴ ተጨፍልቀው ስለሚታዩ። ዋጋ ለማረጋጋት ስራ መሥራት ይገባናል ብለን እዚህ ፓርላማም አንስተን ሰፊ ስራ ተሰርቷል። ለምሳሌ የሰንበት ገበያዎችን (የእሁድ ገበያ) ቁጥር ከሁለት ሺህ በላይ ማድረስ ተችሏል፤ ምርታማነትም በብዙ ሴክተሮች አድጓል። የመንግሥት ድጎማም ተጨምሯል፤ በቅርቡ በነበረው ዓለም አቀፍ ሁኔታ ነዳጅን በወር በ16 ቢሊዮን ብር እንደጉም የነበረውን፣ አሁን 20 ቢሊዮን ብር ጨምረን በወር እስከ 36 ቢሊዮን ብር እየደጎምን እንገኛለን። ይህ ትልቅ አቅም ነው፤ ሌላውን ማዳበሪያ ሳይጨምር በነዳጅ ላይ ብቻ በወር 30 ፕላስ ቢሊዮን ብር መደጎም ቀላል አይደለም። በዚህ ስራ ምክንያት በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ግሽበቱን ወደ 'አንድ አሃዝ' (Single Digit) አውርደን ማሳካት ችለን ነበር፤ ሆኖም ግጭቶች ሲፈጠሩ የመጣው የገቢ ዕቃዎች ግሽበት በኢነርጂና በማዳበሪያ ላይ ተጽዕኖ ፈጥሮ፣ በተለይ በምግብና ምግብ ነክ ባልሆኑ ቁሳቁሶች ላይ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።

 

ኢንፍሌሽን ኢትዮጵያ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሊቀር አይችልም፤ 10% የኢኮኖሚ እድገት እያመጣን ግሽበቱን ዜሮ ማድረግ አንችልም፣ እሱን መጠበቅ የለባችሁም። ጤናማ በሆነ መንገድ ከአንድ አሃዝ (Single Digit) ጋር የሚሄድና ከእድገታችን ጋር የሚመጣጠን ከሆነ አይቀሬ ነው። ዋናው ችግር የኑሮ ውድነት (Living Cost) እና የሰዎች በገቢያቸው ህይወታቸውን የመደጎም አቅማቸው ውስን መሆኑ ነው። ለዚህም የሰዎችን ገቢ ለማሻሻል በጣም ብዙ ስራ ይጠብቀናል። የኢትዮጵያን አነስተኛ የደሞዝ ወለል (Minimum Wage) በተለይም በግሉ ዘርፍ ያለውን መመርመርና ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልጋል። መደበኛ ባልሆነው (Informal) ገበያ ውስጥ ከፍተኛ ክፍያ ያለ ቢሆንም፣ ሥርዓት ስላልያዘ ሕግ ሊበጅለትና ሊቆጣጠሩት ይገባል።

 

ቅድም እንዳነሳሁት፣ ሰዎች በትርፍ ህዳግ (Profit Margin) ላይ ሊያስቡበት ይገባል። ለትዝብት ያህል፣ አንዳንድ የስራ መስኮችን ብንመለከት፤ ለምሳሌ አቶ ታገሰ ሻይ ቤት ካላቸው፣ ሄዳችሁ 'ገበያ እንዴት ነው?' ብትሏቸው፣ 'ገበያ የለም፣ ታክስ በዛብን፣ ሰራተኛ እንደዚህ ሆነ' ይሏችኋል። በሳምንቱ ግን 'ሁለተኛ ብራንች ከፍቻለሁ፣ ና መርቅልኝ' ይላሉ። በብዙ ሴክተሮች ያሉ ሰዎች 'ወጪ በዛብን፣ ታክስ በዛብን' እያሉ ነገር ግን ብራንቾችን ሲጨምሩ ታያላችሁ፤ ወጪ ከበዛና ገቢ ከሌለ ብራንች መክፈት አያስፈልግም ነበር፣ ስራውን መተው ነበር የሚያስፈልገው። ይህ በሱቅም፣ በሻይም፣ በሁሉም ይታያል። ነጋዴዎችን እንፈልጋቸዋለን፣ አንጠላቸውም፤ ግን ለአይን ማረጋገጫ እንዲሆናችሁ እዚህ ከተማ ውስጥ የሚነዱ ዘመናዊ መኪናዎችን ተመልከቱ። ገቢ የሌለውና እድገት የሌለው ሰው እንደነዚህ አይነት መኪናዎችን እንዴት ሊነዳ ይችላል? እንደተባለው በድሃውና በሀብታሙ መካከል ያለው ልዩነት (Gap) እየሰፋ እንዳይሄድ ሁነኛ እቅድ አውጥተን መስራት ይኖርብናል። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች፣ የፓርላማ አባላትን ጨምሮ፣ ይቸገራሉ፤ ይህንን ማሰብ ያስፈልጋል። ይህ ጉዳይ በስትራቴጂያችን ውስጥ እንደ አንኳር ጉዳይ ተይዞ እየታሰበበት ነው። ክቡር ዶክተር ደሳለኝ እንዳሉት እኛም አበክረን እንሰራለን፣ የእነሱንም ድጋፍ እንፈልጋለን። የሰዎቻችን ኑሮ መሻሻል አለበት፣ ገቢ ማደግ አለበት፣ ከእድገቱ እኩል ሁሉም የሚቋደስበት ሥርዓት መኖር አለበት፤ በዚህ ላይ ምንም ጥያቄ የለም፣ ትክክለኛ ሀሳብ ነው።

 

እዛው ላይ ግን፣ እናንተ የገጠር ልጆች፣ ቁጥሩ አነስተኛ በመሆኑ ለፉከራና ለጉራ ባይበቃም፣ ገጠር ስትሄዱ ሶላርና ባዮጋዝ የሚጠቀሙ፣ ቲቪ ያላቸውና ሞባይል ቻርጀር የሚጠቀሙ አባትና እናቶችን ማየት ትችላላችሁ። ይህም ሀብቱ በከተሞች ብቻ ሳይሆን ወደ ገጠርም እየገባ መሆኑን ያሳያል። የገጠር ኮሪደር ስራን ብትወስዱ፣ አምናና ካቻምና እኛ እየገነባን አናስመረቅም ነበር፤ ዘንድሮ አርባምንጭ ሄጄ አርሶ አደሮች በራሳቸው አቅም፣ ዲዛይንና አነስተኛ ድጋፍ ተደርጎላቸው የገነቧቸውን ቤቶች ስመለከት በጣም ተስፋ ሰጪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ርግጥ ነው፣ እዚያ ያየኋቸው ጥቂት ናቸው፤ አሁንም በስፋት መቀጠል አለበት። ነገር ግን ታች ያለው ሰው የእድገቱ ተቋዳሽ እንዲሆን በብዙ መልኩ ሙከራ እየተደረገ ነው። ብዙ ማሳያዎች አሉኝ፣ ጊዜያችሁን ላለመውሰድ እተወዋለሁ። ጥንቃቄና ተጨማሪ ስራ ያስፈልጋል፤ እድገታችን ሁሉንም አካባቢ መንካትና ሁሉንም ዜጋ በየደረጃውና በልፋቱ ልክ ተጠቃሚ ማድረግ አለበት። ያ ካልሆነ፣ ያመጣነው ውጤት ተመልሶ እኛን ይበላል፤ አደገኛ ነገር ስለሆነ ውጤቱን አስተካክሎ መግራት ያስፈልጋል። አገራችን ወደኋላ እንዳትቀር ተጋግዘን የሚቻለውን ሁሉ እናደርጋለን።

 

ቤት ግንባታን በሚመለከት፣ አንዱ ስብራት ብለን ካነሳናቸውና እንደ ጋዝ፣ ማዳበሪያና ኤርፖርት ካሉ ትላልቅ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሀውሲንግ (Housing) ነው። 'ባለፉት ዓመታት ከ1 ሚሊዮን በላይ ቤት እንገነባለን' ብለን አቅደን ነበር፤ ታስታውሱ እንደሆነ ባለፉት ሰባት ዓመታት በአጠቃላይ 1.2 ሚሊዮን ቤቶችን ገንብተናል። አሁን ግን እቅዳችንን አሻሽለን በዚህ አምስት ዓመት ውስጥ ቢያንስ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት አቅደናል። ይህ በምን ይከናወናል? በመንግሥት፣ በግልና በመንግሥት-ግል አጋርነት (PPP) በተለያዩ መንገዶች ይገነባል። ያንን ለማድረግ ፖሊሲ ተቀርጾ በካቢኔ ፅድቋል። የ3ዲ (3D Printing) ቴክኖሎጂን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እያስገባን ነው። የኮንስትራክሽን ግብዓት ፋብሪካዎች አብዛኛዎቹ ተጠናቀው ምርት እየጀመሩ ነው፤ ሰልጣኞችም ስልጠና ወስደው እየተዘጋጁ ነው። በሁሉም ክልሎች በገጠርና በከተማ እንቅስቃሴዎች አሉ፤ እነሱን አጠናክረን በዚህ አምስት ዓመት 1.5 ሚሊዮን ቤት እንገነባለን። ለዚህም የሞርጌጅ (የቤት ብድር) ሥርዓት እያበጀን ነው። ሰዎች ቤት መግዛት ካልቻሉ እንዴት በቅናሽ መከራየት ይችላሉ? እንዴት ከገቢያቸው ላይ እየከፈሉ በረጅም ጊዜ የቤት ባለቤት መሆን ይችላሉ? የሚለውን ጉዳይ መንግሥት እየሰራበት ይገኛል። ተባብረን ማሳካት የሚገባን ትልቅ ፕሮጀክት ነው፤ ቤቶች የኑሮ ዘይቤያችንን ከመቀየር ባለፈ ሰፊ የስራ ዕድል ይፈጥራሉ፣ ኢኮኖሚውን ያነቃቃሉ። ስለዚህ እንደማንኛውም አንኳር ፕሮጀክት ተወስዶ የሚሰራ ይሆናል።

 

ፕሮጀክቶችን በሚመለከት ብዙ ጉዳዮች ተነስተዋል። ፕሮጀክቶች ላይ ሰፊ ጥረቶች ይደረጋሉ፤ ለምሳሌ በዚህች ሁለትና ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ ሰባት አዳዲስ ኤርፖርቶችን ገንብተን አጠናቀናል። ለረጅም ጊዜ ቆመው የነበሩ በርካታ ግድቦች፣ ለምሳሌ የመገጭና የአርጆ ግድቦች በዚህ ክረምት ይጠናቀቃሉ። በአፋር፣ በሶማሌና በባሌ ክልሎች ትላልቅ ግድቦችን ጨርሰን ስናስመርቅ አይታችኋል፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብንም በከፍተኛ ደረጃ አድርሰናል። በከተማ ደረጃ፣ በአዲስ አበባ ብቻ ባለፉት አጭር ጊዜያት ከ1000 ኪሎ ሜትር በላይ አስፋልት ሰጥተናል። በኢትዮጵያ አጠቃላይ የመንገድ ፍላጎትን ለማሟላት ቢያንስ 2 ትሪሊዮን ብር ያስፈልጋል፤ የእኛ አጠቃላይ አመታዊ በጀት ደግሞ 2 ትሪሊዮን ብር አካባቢ ነው። ስለዚህ መንገድ ብቻ ሰርተን ሌላውን መተው አንችልም።

 

በርካታ ፕሮጀክቶች በተሳኩበት ልክ የሚጓተቱ ደግሞ አሉ፤ አንደኛው ምክንያት ከካሳ (Compensation) ክፍያ ጋር የተያያዘ ነው፤ የቀበሌና የወረዳ አመራሮችና የተወሰኑ ነጋዴዎች ባላቸው ጥቅምና ስብጥር፣ ከፕሮጀክቱ ዋጋ በላይ በካሳ ለመጠቀም በሚያደርጉት ጥረት ፕሮጀክቶች ይስተጓጎላሉ። ሌላው ደግሞ የፋይናንስ ምንጩ ሳይታወቅና በጀት ሳይያዝ ዝም ብሎ ፕሮጀክቶችን ይፋ (Announce) ማድረግ ነው። ለምሳሌ በየሄዳችሁበት ክልል፣ እግረ መንገዱን ትምህርት እንዲሆን፤ ኃላፊዎች ለተለያየ ስራ ሲሄዱ አንዳንድ ሰዎች ሆን ብለው ሽማግሌዎችን ያደራጃሉ፣ ሳር እያስያዙ ወረዳና ዞን ያሉ ሰዎችን 'ይህንን ፕሮጀክት ጠይቁ' ይላሉ። ያ ኃላፊ ልክ ከኪሱ አውጥቶ እንደሚሰጣቸው ነገር ማለት ነው። ይህ መጥፎ ባህል ነው፤ አቅደን፣ ጥያቄዎቹን ለይተን፣ በቅደም ተከተል (Priority) አስቀምጠን መስራት አለብን እንጂ በየመንገዱ ቃል የሚገባ ከሆነ የነበረውን ችግር እንደግማለን። እንደዛ አናደርግም፣ በየመንገዱ ቃል አንገባም፤ የጀመርነውን ለመጨረስ ነው ጥረት የምናደርገው። በጣም ብዙ ፕሮጀክቶችን አሳክተናል፣ የቀሩንም አዋጭነታቸው እየታየ በቅደም ተከተል በቤኒሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የአመራር ድጋፍ የሚፈልጉትን ባለን ውስን አቅም ልክ እየደገፍን እንሄዳለን። ነገር ግን የፕሮጀክት አፈጻጸም እውነት ለመናገር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በዚህ ዘመን እንዳለው አይነት የስራ ክትትልና ቁጥጥር ያለ አይመስለኝም፤ ምክንያቱም በቴክኖሎጂ ታግዘን በርቀት ጭምር (Remote Follow-up) ስለምንከታተልና ስለምንመራ፣ ክትትሉ ጠንከር ያለ በመሆኑ ከፍተኛ መሻሻል አለ። ለምሳሌ ቤኒሻንጉልን ብንወስድ፣ አስሶሳ ላይ እንደምታውቁት የአምናውና የዘንድሮው አፈጻጸም አንድ አይደለም፤ በቂ ነው ወይ ከተባለ አይደለም ግን ለውጦች አሉ። በየቦታው የቆሙ ፕሮጀክቶች፣ ለምሳሌ የደባርቅ-ጎንደር መንገድ ወይም መገጭ ላይ ችግሮች ነበሩ፣ አሁን ግን መሻሻሎች አሉ። ባሌም እንዲሁ ለውጦች አሉ። ብዙ የሚቀሩ ጉዳዮች ስላሉ ተባብረን ለመከወን እንሞክራለን፤ የመንግሥት ዋና ስራ ፍላጎትና አቅምን እያመጣጠነ የህዝባችንን ኑሮ ከፍ ማድረግ ይሆናል።

 

የዘንድሮውን በጀት በሚመለከት፣ አንደኛ በተቻለ መጠን ወጪ ቆጣቢ መሆን አለብን። ወጪ መቆጠብ ይኖርብናል። በጀት 1.1 ወይም 1.2 ትሪሊዮን ሲባል በልጽገን የጨረስን መምሰል የለበትም፣ ገና ነን፤ ብዙ እዳና እጥረት አለብን። ሁለተኛ፣ ክልሎች ከፌደራል መንግሥት ዝም ብሎ የሚፈስ ሀብት እንዳለ መጠበቅ ሳይሆን የራሳቸውን ገቢ ማመንጨት መጀመር አለባቸው። ለምሳሌ አዲስ አበባን ብንወስድ፣ ከለውጡ በፊት የነበራት የገቢ አቅም ልክ ለመናገር ያሳፍራል፤ በዚህ ዓመት ግን ከ335 እስከ 340 ቢሊዮን ብር ገቢ አስገብታለች። 340 ቢሊዮን ብር ማለት ሪፎርሙ ከመምጣቱ በፊት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትም በአንድ ላይ የማይሰበስበው መጠን ነበር። በሁሉም ክልሎች ገቢ እንዲሻሻልና በዚያ ልክ ልማት እንዲመጣ ጥረት መደረግ አለበት። ከዚህ በተጨማሪ ዲሲፕሊን ያስፈልጋል፤ ስራ በትጋት፣ በድካምና በዲሲፕሊን ካልተመራ አይከናወንም፤ እያንዳንዱ ሪሶርስ በአግባቡ መመራት አለበት። በግሉ ሴክተር የተሰማሩ ኩባንያዎችም ራሳቸውን እንደ ነጋዴ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ገንቢ ማየት አለባቸው፤ 'ተገኝቶ መዝረፍ' ሳይሆን ጥራት ያለውና ለልጆቻችን የሚሸጋገር ነገር መስራት ላይ ማተኮር አለባቸው። ወደ ክልሎች የወሰናችሁት የኤስዲጂ (SDG) በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን በጥብቅ መቆጣጠር አለብን፤ ዝም ብሎ ሰጥቶ መተው አይሰራም፣ የተሰጠው ሀብት ለዚያው ስራ መዋሉ መረጋገጥ አለበት።

 

ሚቀጥለው ዓመት በጣም ከፍተኛ ስራ የሚጠብቀን ዓመት ነው። እስካሁን ከነበረን ፈተና በላይ፣ እስካሁን ካገኘነው ድል በላይ የሚጠበቅበት ዘመን ነው። አሁን ከለፋነው በላይ ለፍተን ውጤት ማምጣት ይጠበቅብናል። ቀደም ሲል እንዳነሳሁት፣ መንግሥታችን የ25 ዓመት እቅድ (Grand Strategy) አዘጋጅቷል። ያንን ግራንድ ስትራቴጂ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በየደረጃው የምናየው ይሆናል፤ መቼ ምን እንደምናሳካ ግልጽ ፍላጎትና ግልጽ አቅጣጫ አስቀምጠናል። የምንፈልገውን እናውቃለን፣ የምንጓዝበትን መንገድ እናውቃለን። ያንን ለመፈጸም የሚያስችል አቅምና ቁርጠኝነት (Commitment) ግን ከሁላችንም ይጠበቃል፤ ከብልጽግና ብቻ ሳይሆን ከሁላችንም። በሚቀጥለው መንግሥት ምስረታ ላይ በተቻለ መጠን ሻል ያለ ቁመናና ብቃት ያላቸው፣ ኢትዮጵያን ማገልገል የሚችሉ የእኛም የሌሎችም ወገኖች የሆኑ ሰዎችን አካተን፣ ተባብረን፣ እየተከራከርን ግን በጋራ እየሰራን ኢትዮጵያን ለማበልጸግ የምንጥር ይመስለኛል።

 

ሌብነትን በሚመለከት፤ ሌብነት ጥዩፍና ቆሻሻ ነገር ነው፤ ግን ሰው እንደሚፎክረው አይደለም። ስብሰባ ላይ 'ሌብነት አለ' ይባላል እንጂ፣ ለምሳሌ ኦዲት በአንድ ሰው ላይ የተጣራ ሪፖርት አምጥቶ፣ መንግሥት ውሳኔ አልወሰደም ካለ እኔ ኃላፊነት እወስዳለሁ። በጥቅሉ ዝም ብሎ ፓርላማ '50 ብር ጉድሏል' አለ፣ የት ጎደለ? ማረጋገጫው ምንድን ነው? በተጨባጭ ማስጠየቅ የሚያስችል መረጃ መኖር አለበት፣ ይህ አንደኛው ጉዳይ ነው። ብዙ አሉባልታዎች አሉ፤ አሉባልታዎች ሁለት መነሻ አላቸው። አንደኛው፣ ሻል ያለ ስራ የሚሰራና ብቁ የሆነ ሰው ከሆነ፣ እሱን ማጥቂያው ቀላሉ መንገድ ስም ማጥፋት በመሆኑ የሚዘምቱ ሰዎች አሉ። እናውቃለን እሱን። ሁለተኛው ደግሞ፣ መንግሥትና ህዝብ አደራ ብሏቸው፣ አምኗቸው እዚህ አቁሟቸው፣ ቃለ መሐላ ገብተው ነገር ግን ከዚህ ምስኪን ህዝብ የሚያጨረብሩ አጭበርባሪዎች ደግሞ አሉ። የቸገረን እኛ መለየቱ ነው፤ በመላምት (በግምት) ከሆነ ውሳኔ የምንወስደው፣ የሚሰራውንና የሚሰርቀውን ቀላቅለን እናጠፋለን። ስለዚህ መላምት ሳይሆን የተጨበጠ መረጃ ይኑር። ከእናንተ ከፓርላማ አባላት ውስጥ፣ በግልጽም ባይሆን የሚጨበጥ መረጃና ደብዳቤ ካላችሁ፣ ጽፋችሁ ለአፈ ጉባኤ ቢሮ ላኩልኝ፤ ያ መረጃ እውነት ሆኖ እርምጃ ካልወሰድን እኔን ጠይቁኝ። 'እገሌ ይህንን ሰርቋል፣ ይህንን አድርጓል፣ ሀብቱን እዚህ ቦታ አስቀምጧል' የሚል ማስረጃ ካላችሁ ላኩ፤ እርምጃ ካልተወሰደ እኛ እንጠየቃለን። በጥቅሉ ግን ዝም ብሎ መኳነን ጠቃሚ አይደለም። ደጋግሜ እንዳነሳሁት፣ 'ኢንስቲትዩሽናል' (በመዋቅር ደረጃ የተደራጀ) ሌብነት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፤ ቢኖር ኖሮ 1.5 ትሪሊዮን ብር ገቢ አይሰበሰብም ነበር። ግለሰቦች ሌቦች አሉ፣ እውነት ነው፤ እነሱን ማወቅ ግን ቀላል አይደለም፣ ሰው 'ሌባ አማክሬ ጠበቃ ይዤ ልስረቅ' ብሎ አይደለም የሚሰርቀው። ያንን ማስረጃና መረጃ ማግኘት በሕግም ይሁን በአድሚኒስትሬሽን እርምጃ ለመውሰድ ያግዛል። ሌብነት ክፉ ነገር መሆኑን አምነን፣ እያንዳንዱ ሰው መጀመሪያ ራሱ ላይ 'ፋይት' ያድርግ፤ አልፎ ሲሄድ ደግሞ በሕግ መጠየቅ የሚያስችል ማስረጃ መያዝ ጠቃሚ ይሆናል። በዚህ አካሄድ ብንሄድ፣ የቀረበው በጀት የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ መትጋት የምንችል ይመስለኛል።

 

በድጋሚ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት የብልጽግና አባላትም ሆናችሁ ከብልጽግና ውጪ፣ በዚህ በተከበረው ምክር ቤት ሀገራችሁን ያገለገላችሁ ጀግኖች፣ ኢትዮጵያም መንግሥታችንም አብዝቶ ያመሰግናችኋል። የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ሆናችሁ በምክር ቤቱ የነበራችሁ ብርቱ ሰዎች፣ ሀሳባችሁን በግልጽ ለመናገር የደፈራችሁ፣ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የሞከራችሁና ሀሳባችሁ ምንም ይሁን ምን በቁርጠኝነት ያቀረባችሁ ሰዎች ጀግኖች ናችሁ። ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ የማይናቅ ሚና ተጫውታችኋልና እናንተንም በእጅጉ ማመስገን እንፈልጋለን። ግን ፓርላማ ብቻ አይደለም የትብብር መስኩ፤ ልባችሁንና አእምሮአችሁን አስፍታችሁ አሁን በጋራ እንድንሰራ፣ በተለይ በኮሪደር ስራዎች ላይ አብረን እንድንቆም አደራ እላችኋለሁ።

 

በመጨረሻም፣ ስኬት የሰጠን፣ በእቅዳችን ልክ ውጤታማ እንድንሆንና የ27 ዓመቱን ስራ በአንድ ዓመት እንድንተገብር የረዳን ፈጣሪያችን የተመሰገነ ይሁን! የኢትዮጵያ ብልጽግና እስኪረጋገጥ ድረስ በጋራ የምንቆም እንሁን።

 

የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት አባቶችና ታላላቅ ሰዎች ተጠቅመን፣ በተቻለ መጠን በእስር ላይ ያሉ ሰዎችን ለመፍታት፣ በውጭ ሀገር ያሉትንና ጫካ ያሉትን በይቅርታ ለማስገባት ልባችን ሰፊ መሆን ይኖርበታል። የምንተወውና ይቅር የምንለው ለኢትዮጵያ ሲባል ነው። ለኢትዮጵያ ሲባል ልክ ለውጡን ስንጀምር የነበረውን አይነት አካሄድ (Approach) መከተል ያስፈልጋል። ብዙዎቹ ክፉ ሲናገሩ የምትሰሟቸው ተስፋ ከመቁረጥ የተነሳ ነው፤ 'የእኛ ሁኔታ አይስተካከልም፣ ዕድል የለም' በማለት ነው። ዕድል እንዳለ፣ ተስፋ እንዳለ ካሳየናቸውና አብሮ መስራት እንደሚቻል ካረጋገጥንላቸው ይመለሳሉ፤ ተፈጥሯቸው መጥፎ ስለሆነ አይደለም። ለዛም ልባችን ክፍት ሆኖ አብዛኛዎቹን ለማቀፍና አካታች የሆነው አገራዊ ምክክር (National Dialogue) የተሳካ እንዲሆን፣ ኢትዮጵያ ሰላማዊ ሀገር እንድትሆንና ብልጽግና የተረጋገጠባት እንድትሆን በጋራ መስራትና መኖር የምንችል ሰዎች መሆናችንን ዓለም እንዲያይ ልባችንን ማስፋት ይኖርብናል።

 

ህወሃትም (TPLF) ጭምር ቀልብ ከገዛና አእምሮ ከገዛ፣ ለመነጋገርና ሰላም ለማምጣት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ከሰላም ሙከራ ውጪ ያለው ሌላው ጉዳይ ለእኛ አይጠቅመንም፤ የሚያስፈልገን ብልጽግናና ልማት ነው፤ ለዚህ ደግሞ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናችን ሆኖ እንዲያግዘን በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

 

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር! ብልጽግናን እናረጋግጣለን። በርቱ!

 

አመሰግናለሁ።

Recommended
Bottom Advertisement
Learn More

ተጨማሪ ዜናዎችን ያንብቡ

ማህበራዊ - ሚዲያ

የከይር ታይምስ ዘገባዎችን በሁሉም ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ይከታተሉ